ያለአግባብ በጀት የተጠቀሙ ድርጅቶች ተጨማሪ በጀት ተያዘላቸው

ኢሳት (ሰኔ 7 ፥ 2008)

ባልፈው በጀት አመት ከስድስት ቢሊዮን ብር የሚበልጥ ገንዘብ አላግባብ ተጠቅመዋል የተባሉ መንግስታዊ ድርጅቶች ጉዳያቸው እልባት ሳያገኝ ተጨማሪ በጀት እንዲያዝላቸው መደረጉ ተቃውሞን አስነሳ።

ከሶስት ሳምንት በፊት የጠቅላይ ኦዲት ተቋም የመከላከያ ሚኒስቴርን ጨምሮ ወደ አምስት የሚጠጉ መንግስታዊ ድርጅቶች ከስድስት ቢሊዮን የሚበልጥ ገንዘብን ያለ አግባብ ተጠቅመዋል ሲል ሪፖርት ማቅረቡ ይታወሳል።

በመንግስት በጀት አጠቃቀም ዙሪያ ሪፖርቱን ለፓርላማ ያቀረበው የኦዲት ጽ/ቤት በነዚሁ መንግስታዊ ድርጅቶች የተበጀተ ገንዘብ ያለ አግባብ እንዲባክን ከመደረጉ በተጨማሪ የገባበት ያልታወቀ በቢሊዮን የሚቆጠር ንብረት መኖሩን አስታውቋል።

ጉዳዩ የሚመለከተው አካል የመንግስት ገንዘብን ያለ አግባብ ተጠቅመዋል በተባሉ ድርጅቶች ላይ ህጋዊ እርምጃን እንዲወሰድ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።

ይሁንና የመንግስት በጀትን ያለአግባብ አባክነዋል የተባሉት ድርጅቶች ምንም አይነት ምርመራና እርምጃ ሳይወሰድባቸው ከ2009 በጀት አመት አምና ከተመደበላቸው በጀት ተጨማሪ ገንዘብ እንደተያዘላቸው ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር በቅርቡ ለፓርላማ የቀጣዩን በጀት በተመለከተ ሪፖርትን ያቀረበ ሲሆን፣ በዚሁ መድረክ ያለአግባት ጥቅም ላይ ውሏል የተባለ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ አጀንዳ ሆነ መቅረቡ  ታውቋል።

ፓርላማው የቀረበለትን የኦዲት ሪፖርት ተከትሎ ምንም እርምጃ ሳይወስድ በበጀት አጠቃቀማቸው ግድፈት የታየባቸው ድርጅቶች ተጨማሪ ገንዘብ እንዲመደብላቸው መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አካላት ገልጸዋል።

ተጠያቂነት የሌለው አሰራር ለህዝብና ለመንግስት አደገኛ አካሄድ ነው ሲሉ የተናገሩት እነዚሁ ባለሙያዎች፣ ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግስት አካል ችግሩን በትኩረት መመልከት ይኖርበታል ሲሉ አክለው አስታውቀዋል።

የመከላከያ ሚኒስቴር የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎች መንግስታዊ ድርጅቶች ከስድስት ቢሊዮን የሚበልጠውን ገንዘብ ያለ አግባብ ተጠቅመዋል ተብለው በኦዲት ጽ/ቤቱ የቀረቡ ተቋማት መሆናቸው ይታወሳል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከቀጣዩ 2009 በጀት አመት 274 ቢሊዮን ብር ረቂቅ በጀት ለፓርላማ እንዲፀድቅ ማቅረቡ የሚታወቅ ነው።