ዩክሬን 60 ሺህ ያህል ጠንካራ የመከላከያ ሀይል እንድትገነባ የአገሪቱ ፓርላማ አዋጅ አጸደቀ።

ማጋቢት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አዲሱ የመከላከያ አዋጅ ግንባታ የጸደቀው  ሩሲያ በአወሳጋቢዋ ክሪሚያ  የፊታችን እሁድ ሪፈረንደም ለማካሄድ በተሰናዳችበት ወቅት ነው።

ክሪሚያ በአሁኑ ሰዓት በሩሲያ የጦር ሀይል ስር የምትገኝ ሲሆን፣ በመጪው እሁድ በሚካሄደው ሪፈረንደም ነዋሪዎቿ በሩሲያ ስር መተዳደር እንደሚፈልጉና እንደማይፈልጉ ድምፃቸውን ይሰጣሉ።

ፕሬሲዳንት ቭላድሚር ፑቲን ፦ በየክሬን በተፈጠረው ቀውስ ሩሲያ ተጠያቂ እንዳልሆነች በተደጋጋሚ እየገለፁ ይገኛሉ።

ፑቲን ይህን ቢሉም  የሀያላን አገራት መሪዎች  ጣታቸውን በፑቲን መንግስት ላይ እንደቀሰሩ ናቸው። የጀርመኗ ቻንስለር  አንጀላ ሜርከል ሁኔታዎች ካልተለወጡ ሞስኮ ከፍተኛ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አደጋ ይጠብቃታል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የአሜሪካው ባራክ ኦባማ በበኩላቸው ዋሽንግተን ከዩክሬን ጎን እንደምትቆም በማረጋገጥ፣ ሞስኮ  እጇን እንድትሰበስብ መክረዋል። “ሩሲያ ጎረቤቷን ዩክሬንን እንደ አጋር በመደገፍ ፋንታ ድክመቷን  ተጠቅማ እየበዘበዘቻት ነው” ነው ያሉት ቻንስለር አንጀላ ሜርከል።

የሩሲያ ወታደራዊ ሀይልና  የሩሲያ ደጋፊ የሆኑ  ታጣቂዎች በክሪሚያ ሱሪያ ሰፍረው ይገኛሉ።. የዩክሬን አካል በሆነችው በአወሳጋቢዋ በክሪሚያ ከሚኖሩት ውስጥ አብሳኞቹ የሩሲያ ዝርያ ያለባቸው እንደሆኑ በተደጋጋሚ መገለጹ ይታወሳል።