ጥር ፳፫ (ሃያ ሦስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ሕጻናት አድን ድርጅት ዩኒሴፍ እ.ኤ.አ. 2017 አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያዊያን ሕጻናት ሕይወት ለማትረፍ 110 ሚሊዮን 500 ሺ የአሜሪካ ዶላር ተጨማሪ አፋጣኝ እርዳታይስፈልገኛል ብሎአል። ከዚህ እርዳታ ውስጥ 17.3 ሚሊዮን ዶላር ለስደተኞች እገዛ ይውላል። 9.2 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ሕጻናት እና ቤተሰቦቻቸውን የተመጣጠነ ምግብ፣ የጤና፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ ለትምህርት እና ለቀጣይ ማኅበራዊ ዋስትና አቅርቦት የሚውል መሆኑንም ዩኒሴፍ በሪፖርቱ አመላክቷል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ሕጻናት አድን ድርጅት ዩኒሴፍ በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ አገራት ውስጥ በተለይ በኢትዮጵያ ላይ ትኩረት በማድረግ በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች ነዋሪ በሆኑ ሕጻናት ላይ የሚደርሰውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመታደግ የጤና እና የምግብ አቅርቦቱን በአፋጣኝ ለማቅረብ ዝግጁትን ማጠናቀቁን በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ባለስልጣን ጋሊያን ሜልሶፕ አስታውቀዋል።
ባለፈው ዓመት በኤሊኖ አየር መዛባት ምክንያት ክፉኛ የውሃ፣ የምግብ እጥረት እና በበሽታ ተጠቂ የነበሩ ዜጎች ከ9.7 ሚሊዮን ወደ 9.2 ሚሊዮን ቢቀንሱም የክረምቱ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ አለመዝነቡን ተከትሎ አሁንም 9.2 ሚሊዮን የእርዳታ እጅ ጠባቂ ኢትዮጵያዊያን ሕጻናት ይገኛሉ ብለዋል። የህንድ ውቂያኖስ ሙቀት በፈጠረው የአየር መዛባት አሁን በኢትዮጵያ አፋር፣ ሶማሌ፣ ኦሮሚያ እና በደቡብ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ድርቁ ክፉኛ አደጋ አስከትሏል።
በድርቁ ምክንያት የምግብ እጥረት፣ ተላላፊ በሽታዎችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ዝግ ሆነዋል።
ከጎረቤት አገር ሶማሊያም በድርቅ ተጠቂ የሆኑ 1 ሽህ 325 ሶማሊያዊያን ድንበር ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። ባለፈው ዓመት ብቻ ቁጥራቸው ከ783 ሽህ 401 በላይ የሚሆኑ የደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ ፍልሰተኞች ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው በጥገኝነት ይኖራሉ።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ሕጻናት አድን ድርጅት ዩኒሴፍ በመላው ዓለም በጦርነት እና በድርቅ ምክንያት ሰለባ የሆኑ 48 ሚሊዮን ሕጻናት እንደሚገኙ እና እነዚህን ሕጻናት ሕይወት ለመታደግ 3.3 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ በሪፖርቱ አስታውቋል።