የ528 ሰዎች ክስ ተቋረጠ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 7/2010)

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የፖለቲካ እስረኞችን እፈታለሁ ያለው የሕወሃት አገዛዝ የ528 ሰዎችን ክስ ማቋረጡን ገለጸ።

ከነዚሁ መካከል 413 ክሶች የተቋረጡት ከደቡብ ክልል በጌዲዮና ኮንሶ ዞኖች ሲሆን ቀሪዎቹ 115ቱ ደግሞ ከፌደራል ናቸው።

ከሌሎቹም ክልሎች ጉዳያቸው ተጣርቶ ሲመጣ ክሳቸው ተቋርጦ የሚለቀቁ እንደሚኖሩ ተገልጿል።

የፌደራል ዋና አቃቢ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ከእስር ክሳቸው ተቋርጦ የሚለቀቁት ሕገ መንግስታዊ ስርአቱን በመናድ እንቅስቃሴ ያልተሳተፉና ሌሎችንም መስፈርቶች ያሟሉ ናቸው።

ዋና አቃቢ ሕጉ ጌታቸው አምባዬ ክሳቸው ስለተቋረጠ የፖለቲካ እስረኞች ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚሁም መግለጫ የሚፈቱና የማይፈቱ በሚል በአገዛዙ የተቀመጡ መስፈርቶችን ይፋ አድርገዋል።

አቶ ጌታቸው እንዳሉት ሕገመንግስቱን በሃይል ለመናድ የተንቀሳቀሱ የፖለቲካ እስረኞች አይፈቱም።

በዚሁም መሰረት ሕዝቡ ይፈታሉ ብሎ የጠበቃቸው የተወሰኑ የፖለቲካ እስረኞች ላይፈቱ እንደሚችሉ የአቶ ጌታቸው አምባዬ መግለጫ አመላክቷል።

ሕገመንግስት በሃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል፣መፈንቅለ መንግስት ለማድረግም ሞክረዋል ተብለው የተፈረጁና የታሰሩት ጂኔራል ተፈራ ማሞ፣ጄኔራል አሳምነው ጽጌና የመሳሰሉት እንደነበሩ ይታወሳል።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌም በዚሁ ክስ ተፈርጀው ሞት የተፈረደባቸውና አሁንም ከየመን ታፍነው በእስር ላይ የሚገኙ ናቸው።

በዋና አቃቤሕጉ መግለጫ መሰረት በጸረ ሽብር ሕጉ ተከሰው መስፈርቱን የሚያሟሉ ሰዎች ግን በ2 ወር ጊዜ ውስጥ ተጣርቶ በይቅርታና በምህረት ሊፈቱ የሚችሉበት ሁኔታ ይኖራል።

እናም በጸረ ሽብር ሕግ ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙት አንዱአለም አራጌ፣እስክንድር ነጋና ውብሸት ታዬን የመሳሰሉት የፖለቲካ እስረኞች ሊፈቱ እንደሚችሉ መግለጫው አመላክቷል።

በአቶ ጌታቸው አምባዬ መግለጫ መሰረት የወጡትን መስፈርቶች አሟልተው የሚገኙ እስረኞች ከሁለት ቀናት ስልጠና በኋላ ይፈታሉ።

ከነዚሁም መካከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፈሃል ተብለው የተከሰሱት ዶክተር መረራ ጉዲና እንዲሁም በልዩ ልዩ ወንጀል የተከሰሱት አቶ በቀለ ገርባና የኦፌኮ አመራሮች ክሳቸው መቋረጡን በሀገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ናቸው።

በዋና አቃቤ ህጉ መስፈርት መሰረት ክሳቸው አይቋረጥም ወይንም አይፈቱም ከተባሉት መካከል በኢኮኖሚ አውታሮች ላይ ጉዳት ያደረሱ፣የሰው ሕይወት ያጠፉና የአካል ጉዳት ያደረሱ እንዲሁም በስርአቱ ተጠቃሚ ሆነው በሌሎች ገፋፊነት ወደ አመጽ የገቡ የሚሉትም ይገኙበታል።

የወልቃይት ማንነት ጥያቄ በማንሳት ወንጀል ሰርተዋል ተብለው የተከሰሱት እነ ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ በምን መልኩ እንደሚፈረጁ ገና ግልጽ አልሆነም።

በይቅርታና በምህረት ደረጃውን ጠብቀው በ2 ወራት ውስጥ ይፈታሉ የተባሉ እስረኞች እነማን እንደሚሆኑም በዝርዝር የታወቀ ነገር የለም።

ሒደቱ ግን በ3 ዙሮች የሚከናወን መሆኑን ዋና አቃቢ ሕጉ አቶ ጌታቸው አንባዬ ገልጸዋል።