ኢሳት (ሰኔ 6 ፥ 2008)
የትምህር ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚሰጥበት ቀን ለሁለተኛ ጊዜ አራዘመ።
ሚኒስቴሩ የፈተናው መሰረቅን ተከትሎ ብሄራዊ ፈተናው ከሰኔ 27 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓም እንደሚካሄደ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ይሁንና የኢትዮጵያ ኣስልምና ጉዳዮች ጠቅላላ ምክር ቤት የፈተናው ጊዜ ከረመዳን ጾም ጋር የተገናኘ ነው ብሎ ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ፈተናው ለሁለተኛ ጊዜ እንዲራዘም መደረጉን ገልጿል።
ለሁለተኛ ጊዜ እንዲራዘም በተደረገው የጊዜ ሰሌዳ መሰረተም የብሄራዊ መልቀቂያ ፈተናው ከሃምሌ 4 ቀን እስከ ሃምሌ 7 2008 አም ድረስ እንደሚሰጥ ታውቋል።
የብሄራዊ ፈተናው በመሰረቁ ምክንያት ከ200 ሺ የሚበልጡ ተማሪዎች ከፈተናቸው የተስተጓጎሉ ሲሆን፣ መንግስት ከ200 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ኪሳራ እንደደረሰበት ለመረዳት ተችሏል።
ለፈተናው በዝግጅት ላይ የነበሩ ተማሪዎች በበኩላቸው መንግስት ፈተና የሚሰጥበትን ቀን በአግባቡ ሳያጤን የሚሰጠው ውሳኔ በጥናት ፕሮግራማቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን የገለጸው ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የትምህርት ሚኒስቴር መሰል ችግሮች ዳግም እንዳይፈጠሩ አስፈላጊው ሁሉ በመደረጉ ተማሪዎች በድጋሚ ፈተናው በቂ ዝግጅትን እንዲያደርጉ ጠይቋል።
በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ተማሪዎች ከኦሮሚያ ክልል ጋር በተገኛኘ ተቀስቅሶ በነበረው ተቃውሞ ትምህርት በአግባቡ ባለመሰጠቱ ብሄራዊ ፈተናው እንዲራዘምላቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
በኦሮሚያ ክልል ተቀስቅሶ በነበረው በዚሁ ተቃውሞ በርካታ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው የቆዩ ሲሆን፣ ከተቃውሞ ጋር የተጠረጠሩ ተማሪዎችም ለእስር ተዳርገው መቆየታቸውን ፖሊስና የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።