መጋቢት ፯(ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአሉ በአውስትራልያ ክዊንስላንድ ግዛት ነዋሪ በሆኑ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እሁድ መጋቢት 7 ቀን 2007 ዓም ተከብሯል። በበአሉ ላይ በግዛቱ ነዋሪ የሆኑ በርካታ ኢትዮጵያውያን የተገኙ ሲሆን የአድዋን ድል ታሪካዊነትን የዳሰሰ ሰፋ ያለ ዝግጅት ለታዳሚው ቀርቧል:: ዓድዋን አስመልክቶ በፕሮጀክተር በታገዘና በምስልና ድምጽ የተደገፉ ማስረጃዎች በቀረቡበት በዚህ ዝግጅት ላይ የዓጼ ምንሊክን አስተዋይነት የቴጌ ጣይቱ ብልህነትና የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ቆራጥነትና አልበገር ባይነት ታዳሚውን ባስደመመ መልኩ ቀርቧል::
በዝግጅቱ ላይ ሌላው ለየት ብሎ የተስተዋለው የእድሜና የጾታ ተዋጾ የታየበት የመድረክ አቀራረቡ ሲሆን ፣ በተለይ የነገ ተረካቢ የሆኑት ወጣቶች በዚህ ዝግጅት ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸው ይበል የሚያሰኝና ሊበረታታ የሚገባው እንደሆነ ከታዳሚዎች ለመረዳት ተችሏል:: በዝግጅቱ ላይ ሌላው ቀርቦ የነበረው የሽለላና ፉከራ ድራማዊ ትእይንት ሲሆን ጀግኖች አባቶቻችን የሃገርን መደፈር በሰሙ ጊዜ ያሳዩትን ቁጣና እምቢ ባይነትን የሚያወሳ ነበር::
ይህም ትእይንት ዝግጅቱን ከማድመቁ በላይ ለወጣቶች የኢትዮጵያን ነባር ባህልንና ማንነትን የማውረስ አንዱ አካል መሆኑን ኤልሳቤጥ ግዛው ከአውስትራሊያ ዘግባለች።