(ኢሳት ዜና–ሕዳር 12/2010)በደቡብ ኢትዮጵያ ሞያሌ አካባቢ የሰፈረው 10ኛ ክፍለ ጦር አባል የሆኑ ቁጥራቸው ያልታወቀ ወታደሮች ከነመሳሪያቸው ትላንት መሰወራቸው ታወቀ።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት የተሰወሩበትን ወታደሮች ለማግኘት ዛሬ ረፋድ ላይ የተጀመረው ፍለጋ መጠናከሩና ኬንያ ድንበር መድረሱም ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የ10ኛ ክፍለ ጦር 1ኛ ብርጌድ ውስጥ ከሚገኙ ሶስት ሻለቃዎች ከአንዱ የተውጣጡትና ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቀው ወታደሮች ለአሰሳ የወጡት ትላንት ሰኞ ህዳር 11/2010 ከሰአት በኋላ መሆኑ ታውቋል።
ይህ ሙሉ መሳሪያ ታጥቆ ለአሰሳ የወጣው ቡድን ከማዘዣ ጣቢያው ጋር ያለው የሬዲዮ ግንኙነት መቋረጡን ተከትሎ ዛሬ ማክሰኞ ከፍተኛ አሰሳ ተጀምሯል።
ለአሰሳ ወጥቶ ከነመሳሪያው የተሰወረውን ቡድን ፍለጋ ዛሬ ረፋድ ላይ ለአሰሳ የወጣው የ10ኛ ክፍለ ጦር ሌላ ሃይል ወደ ኬንያ ድንበር መንቀሳቀሱም ታውቋል።
ሰራዊቱ ወደ ኬንያ ድንበር ከማቅናቱ በፊት በቦረናና ያቤሎ ፍተሻ ማድረጉም ተመልክቷል።
ወታደሮቹ በቁጥር ምን ያህል እንደሆኑ የታወቀ ነገር የለም።-የተሰወሩበትም ምክንያት ግልጽ አልሆነም።
ከተሰወሩት ወታደሮች ውስጥ በቅርቡ የማዕረግ እድገት ያገኙ እንደሚገኙበትም ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።