የ 1 ዶላር ምንዛሬ ለማግኘት 1 ብር ከ 25 ሳንቲም ጉቦ መክፈል ግድ ነው ተባለ

ጥቅምት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከወጋገን ባንክ በስተቀር በአብዛኞቹ የአገሪቱ ባንኮች የውጪ ምንዛሬ በመጥፋቱ፤  ምንዛሬ ፈላጊዎች  በእያንዳንዷ ዶላር  1 ብር ከ 25 ሳንቲም ጉቦ  እንዲከፍሉ መገደዳቸው  ተዘገበ።

 

በዚህም መሰረት አንድ ሰው የአንድ መቶ ሺ ዶላር ምንዛሪን ለማግኘት፤  ለምናዛሬ ፈቃጅ አካላቱ እስከ 125 ሺ ብር  ጉቦ መክፈል ግዴታው ሆኗል።

 

በቅርቡ የተከሰተውን የውጪ ምንዛሬ እጥረት በመጠቀም የአንዳንድ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች አግባብ ያልሆነ ሥራን እየሰሩ መሆኑን  የገለጹት አስመጪ ነጋዴዎች፤በዚህ ዙሪያ የሚታየውን ችግር የሚመለከተው አካል እንዲፈትሸው አመልክተዋል።

 

በጉዳዩ ዙሪያ  የብሔራዊ ባንክን ምላሽን ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አለመሳካቱን የሰንደቅ ዘገባ ያመለክታል።

 

የውጪ ንግድ በተለይም የቡና እና የሰሊጥ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ መውደቁ  እንዲሁም  የ አቶ መለስን መታመም ተከትሎ እስከ ቀብራቸው ጊዜ ድረስ ለረዥም ጊዜ ሁሉም ነገር  መቆሙ ለውጪ ምንዛሪ እጥረቱ ዋነኛው ምክንያት ነው።

የመንግስትና ሁሉም የግል ባንኮች በምንዛሬ እጥረት እየታመሱ ባሉበት በአሁኑ ወቅት የወጋገን ባንክ ብቻ ያለ ምንም ችግር ለደንበኞቹ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ላኪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።

 

በርካታ ላኪዎች የውጪ ምንዛሬ ለማግኘት ከ አራት እስከ ስድስት ወራት ጠብቁ እየተባሉ ሥራቸውን እስከማቆም ደረጃ በደረሱበት በአሁኑ ጊዜ የወጋገን ባንክ ደንበኞች የሆኑ  ነጋዴዎች ግን በወር ውስጥ ሁለትና ሾስት ጊዜ ድረስ ዕቃ ከውጪ እያስገቡ መሆናቸውን ላኪዎቹ  ጠቁመዋል።

የምንዛሬ ችግሩ አሣሳቢ ደረጃ ላይ ከደረሰ ወራት የተቆጠሩ ቢሆንም፤መንግስት ግን በጉዳዩ ላይ ምንም ነገር አለማለቱ በተለይ በላኪና አስመጪነት በተሰማሩ ነጋዴዎች ዘንድ አግራሞትን ፈጥሯል።