የፕሮቴስታንት ሀይማኖት ተከታዮች እየተሳደድን ነው አሉ

ሐምሌ ፲፮(አስራ ስድስት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሰሜን ወሎ ዞን ከወልድያ ከተማ በ140 ኪሜ ርቅት ላይ በትምገኘዋ መቀት ወረዳ የሚገኙ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ከፍተኛ እንግልት እደረሰባቸውና አካባቢውንም ለቀው እንዲወጡ ግፊት እየተደረገባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁን በደረሰን መረጃ 10 የሚሆኑ የሀይማኖቱ ተከታዮች አካባቢውን ለቀው የወጡ ሲሆን፣ አንድ ተመስገን የተባለ ወጣት ለተባባሪ ዘጋቢያችን እንደገለጸው አማኞቹ ድንጋይ ይወረወርባቸዋል፣ ቤታቸውም በድንጋይ ይደበደባል። ተመስገን ሀምሌ 1 ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞበት፣ ሞቷል ተብሎ ተጥሎ መትረፉንም ገልጿል።

የኦሮቶዶክስ ሀይማኖት ተከታይ የሆኑት መርጌታ ሙሴ ከፕሮቴስታንት ጋር ባላቸው ቀረቤታ መደብደባቸውን፣ ወርቁ ገበየሁ የተባለ ሰውም እንዲሁ ድብደባ ተፈጽሞበት እጁን መሰበሩን ተባባሪ ዘጋቢያችን ተናግሯል።

በወረዳው ውስጥ የሚኖሩ ፕሮቴስታንቶች ቤት ለመከራየትና ስራ ለመስራት አለመቻላቸውን በየጊዜውም እንገድላችሁዋለን የሚል ማስተጠንቀቂያ እንደሚደርሳቸው ለመረዳት ተችሎአል።

ጉዳት የደረሰባቸው መርጌታ ሙሴ ተክለብርሀን “በወረዳው ውስጥ ለህዝብ የሚቆረቆር መንግስት ህግ ባለመኖሩ” ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰነ ነው  ብለዋል።

የወረዳውን አስተዳዳሪ አቶ ይሄነው በላይን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ብንደውልም ስላካቸው አይነሳም።