የፕሬስ ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንቅስቃሴዎች ሽፋን እንዳይሰጥ እያደረጉ ነው ተባለ።

የፕሬስ ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንቅስቃሴዎች ሽፋን እንዳይሰጥ እያደረጉ ነው ተባለ።
(ኢሳት ዜና ሰኔ 22 ቀን 2010 ዓ/ም) ይህን ያሉት፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሠራተኞች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ግልጽ የአቤቱታ ደብዳቤ ላይ ነው።በአዲስ ዘመን፣ በኢትዮጵያን ሄራልድ፣ በበሬሳ፣ በአል ዓለም ጋዜጦችና በዘመን መጽሄት የሚሠሩ በርካታ ጋዜጠኞች “በድርጅታችን ውስጥ የሚካሄደውን ዓይን ያወጣ ጥላቻና ሳቦታጅ ስለመጠቆም” በሚል ርዕሰ ለዶክተር አብይ አሕመድ በጻፉት ደብዳቤ፣
ድርጅቱ ለስሙ ዋና ስራ አስኪያጅ ለስሙ ቢኖረውም በራሱ ድክመት ኃላፊነቱን በውስጠ ታዋቂ ለምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ አሳልፎ እንደሰጠ በመጠቆም፣ ምክትል ስራ አስኪያጁ አጋጣሚውን በመጠቀም የፕሬሶቹን ዋና አዘጋጅነት ቦታዎችን ጨምሮ ቁልፍ ቦታዎች በአንድ ብሔር እንዲያዝ አድርጓል ብለዋል፡፡
“በዚህ ምክንያት የረዥም ዓመት ልምድ፣ ችሎታ፣ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ሰዎች ተገፍተዋል” ያሉት እነኚሁ በርካታ ጋዜጠኞች፣
የፕሬስ ድርጅቱ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ይህም አልበቃ ብሏቸው ዶክተር አብይ አሕመድ ወደሥልጣን ከመጡ በኃላ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የሚገኙ ያኮረፉ ጓደኞቻቸው ጋር እጅና ጓንት በመሆን -ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚመለከቱ የዜና ሽፋኖች በተገቢው ሁኔታ እንዳይስተናገዱ እያደናቀፉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ጋዜጠኞቹ በደብዳቤያቸው እንደጠቆሙት፣ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ አብዛኛውን ጊዜም ምሽቱን የህወሃት አባላትን ብቻ ያካተተ ልዩ ስብሰባ በማድረግ የሚያሳልፉ ሰሆን፣ ይህን ስብሰባ ለምን ዓላማ እንደሚያካሂዱ መረጃው ባይኖረንም አብዛኞቹ ሠራተኞች ሁኔታው ጤናማ አለመሆኑን በመገመት በጥርጣሬ ሲመለከቱት መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
ተቋሙ በተለይ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በየቀኑ እስከ ምሽቱ አራት፣ አንዳንዴም አምስት ሰዓት ድረስ የህወሀት አባላት ብቻ የሚሰበሰቡበት ቢሮ ሆኗል ያሉት ጋዜጠኞቹ፣ ይህ የምክትል ሥራ አስኪያጁ ያፈነገጠ ተግባር የተቋሙ ጋዜጠኞች መነጋገሪያና ሁሉም በንቃት የሚከታተሉት ጉዳይ ከሆነ መሰንበቱን አስረድተዋል፡፡
ጋዜጠኞቹ በደብዳቤያቸው እንደጠቆሙት፣ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ በተለየ መልኩ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚመለከቱ ዘገባዎች እንዳይስተናገዱ ዓይን ባወጣ መልኩ የሚያደርጉት ጥረት ከአብዛኛው ጋዜጠኞች ጋር ግጭት ውስጥ አስገብቷቸዋል።
ጋዜጠኞች በራሳቸው እምቢ ባይነት እስካሁን ትልልቅ ጉዳዮችን በተገቢው ሁኔታ ሽፋን እንዲያገኙ ሲያደርጉ ቢቆዩም፣ ምክትል ሥራ አስኪያጁ በያዙት የተሳሳተ አቋም ሳቢያ በዚህ ሁኔታ ለቀጥሉ የሚችሉበት ዕድል ጠባብ ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን ችግሮች መርምረው አፋጣኝ እርምጃ ይወስዱ ዘንድ ይህን ጥቆማ መጻፋቸውን የገለጹት ጋዜጠኞቹ፣ “ይህን ስንጽፍልዎ የጀመሩት ትግል እንዲሳካ እኛም በያለንበት የአቅማችንን ለመስራት ቃል በመግባት ነው”ብለዋል።