(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 17/2010)
በኢትዮጵያ በተፈጠረው ቀውስ ላይ ማብራሪያ ካልተሰጠን በመደበኛ ስብሰባ አንገኝም ያሉት የፓርላማ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተወያዩ።
በዝግ ለ3 ሰአታት በተካሄደው በዚሁ ስብሰባ 4ቱ የኦሮሚያ፣የአማራ፣የትግራይና የደቡብ ፕሬዝዳንቶች ከአቶ ሃይለማርያም ጋር መገናኘታቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአሜሪካ የሚገኘውን አይጋ ፎረም የሕወሃት ድረ ገጽ ጠቅሶ ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ከፓርላማ አባላቱ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከተጠየቁ በኋላ ምላሽ ሳይሰጡ ሲያቅማሙ መቆየታቸው ታውቋል።
በስተመጨረሻ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባን አቋርጠው ለመገኘት ተገደዋል።
አቶ ሃይለማርያም ከፓርላማ አባላቱ ጋር ያደረጉት ዝግ ስብሰባ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ ያልተፈለገው ከተቆጡት የኦሕዴድና የብአዴን ተወካዮች ጠንከር ያለ ጥያቄ ሊገጥማቸው ይችላል በሚል ስጋት መሆኑን ታዛቢዎች ይናገራሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፓርላማ አባላቱ ጋር ውይይት ካካሄዱ በኋላ ስለ ይዘቱ ከመንግስት በኩል መግለጫ አለመሰጠቱ ጥያቄና መልሱ ጤናማ እንዳልነበር የሚያመላክት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
በፓርላማ ስብሰባው ላይ የአራቱ ክልል ፕሬዝዳንቶች ከምክር ቤቱ የአሰራርና የስነምግባር ደንብ ውጭ እንዲገኙ የተደረገበት ምክንያት በፓርላማ አባላቱ ላይ የስነልቦና ተጽእኖ ለማድረግ ሊሆን እንደሚችልም ግምቶች አሉ።
የክልል ፕሬዝዳንቶች የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት እንጂ የፓርላማ የሕዝብ ተወካዮች አይደሉም።