ነኅሴ ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሩዝ በማምረት የሚታወቀው የፎገራ መስክ ለሸንኮራ አገዳ ተክል ሊውል ነው መባሉን ተከትሎ ፣ ሩዝ በማምረት ኑሮአቸውን የሚገፉ አርሶአሮች ስጋት ላይ ወድቀዋል።
በጣና ሃይቅ ዳር የሚገኘው ሰፊው የፎገራ ረግራጋማ ሜዳ ከማዳበሪያ ነጻ ሆነ ሩዝ በማምረት የሚታወቅ ቢሆንም፣ ገዢው ፓርቲ በአገሪቱ የሚታየውን የስኳር እጥረት ለመፍታት በሚል ሰበብ አርሶአደሮችን በማፈናቀል ቦታውን ለሸንኮራ አገዳ ተከል ለማዋል እንቅስቃሴ ጀምሯል።
ለሸንኮራ ተክል የሚውለውን መሬት የመለካቱ ስራ የተጀመረ ሲሆን፣ በሚቀጥለው አመት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። በአካባቢው የሚመረተው ሩዝ ለበርካታ አርሶአደሮች የህልውና መሰረት ሆኖ ቆይቷል። የሩዝ ምግብ ቀስ በቀስ ተቀባይነቱ እየጨመረ መሄዱን ተከትሎ፣ አርሶአደሮች ከራሳቸው ፍጆታ በተጨማሪ ለገበያ የሚውል ምርት ማምረት ጀምረው ነበር።