(Sept. 8) የፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ፤ አቶ ብዙአየሁ ወንድሙ፤ የግድያ ዛቻ እንደደረሰበት ሲናገር፤ እንዳትታም የተከለከለችውን ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ሕትመትና ህልውና ለመቀጠል፤ “ዘመቻ ነፃነት” የተሰኘ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን በአዲስ አበባ የሚገኙት የጋዜጣዋ ዋና አዘጋጆች ገለፀ።
ምክትል ዋና አዘጋጁ አቶ ብዙአየሁ ከኢሳት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፤ በብርሃንና ሰላም እምቢታ ላለፉት ሁለት ሣምንታት እንዳትታተም የተከለከለችውን ጋዜጣ ህልውና ለመቀጠል፤ ፍትህ ሚኒስትርን ጨምሮ፤ ለተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዳመለከቱና መልስ እየጠበቁ እንደሆነ፤ ጋዜጣው እንዲታተም ካልተፈቀደ ግን፤ እስከ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የሚደርስ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ላይ መለስን የተቸ ጽሑፍ አወጣችሁ በሚል ምክንያትም፤ የተለያዩ ሰዎች እየደወሉ “እንደ ቀይ ሽብር መንገድ ላይ እንደፋሃለን፤ መለስ ከመቀበሩ በፊት አንተን እንገድልሃለን” የሚሉ የተለያዩ የስልክ ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎች እንዳደረጉባቸው ተናግረዋል። ማስፈራሪያው በሌሎች የፍኖተ ነፃነት አዘጋጆች ላይም እንደተደረገ የጋዜጣው አዘጋጆች ገልጸዋል።
ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ባለፈው ሣምንት የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ ባወጣችው ልዩ እትም፤ ኅብረተሰቡ ቅር ተሰኝቷል በሚል ምክንያት፤ እንዳትታተም የተደገረ መሆኑን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፤ ጋዜጣዋ በዚህ ሳምንት ትታተማለች ተብሎ ቢጠበቅም፤ በዚህ ሳምንትም ሳትታተም ቀርታለች።
ከወር በፊት፤ የፍትህ ጋዜጣም የአቶ መለስን ሞት ዘግባ በማውጣቷ ከህትመት መታገዷና እንድትቃጠል የተደረገ ሲሆን፤ የጋዜጣዋ አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ ለሶስት ቀን ታስሮ መፈታቱ ይታወሳል።