ሐምሌ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የፍትህ ጋዜጣን እግድ እንዲያፀድቅ በዐቃቤ ህግ ጥያቄ የቀረበለት የከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት፤ ዛሬ ከሰዓት በሁዋላ ጉዳዩን በዝግ ችሎት በማየት የእግዱን ውሳኔ ተቀብሎ ማፅደቁን አሳውቋል።
ይሁንና ችሎቱ መቼ እንደተካሄደ እና ልደታ ስንተኛው ችሎት ውስጥ እንደተካሄደ ሌላው ቀርቶ የጋዜጣው አዘጋጆች እንኳ እንደማያውቁ፤ ወኪላችን ከአዲስ አበባ ያጠናቀረው መረጃ ያመለክታል።
ፍትህ፤ጠንካራ ትችቶችን በምክንያታዊ ትንታኔ አስደግፎ ለአንባብያን በማቅረብ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚጠቀስ ብቸኛ ነፃና የግል ጋዜጣ ነው።
በፍትህ ጋዜጣ እና በዋና አዘጋጁ በተመስገን ደሳለኝ ላይ አዲስ ዘመንን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስትና የኢህአዴግ ልሳናት ለወራት የዘለቀ ዘመቻ ቢከፍቱባቸውም ከአቋማቸው ሊነቃነቁ ባለመቻላቸው፤ የገዥው ፓርቲ ሹመኞች ወደለየለት የጀብደኝነት እርምጃ በመግባት የባለፈው ሳምንት የጋዜጣው ህትመት እንዲታገድ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የጋዜጣው ህትመት የታገደው ለ 33 ሺህ ጋዜጣ፤ ከ80 ሺህ ብር በላይ ክፍያ ከተፈፀመ በሁዋላ ነው።
የጋዜጣው አዘጋጆች ይህን ዓይን ያወጣ ህገ-ወጥ ውሳኔ በመቃወም አቤት ቢሉም፤ በጉዳዩ ዙሪያ ባልተጠየቁበት እና ሀሳባቸው ባልተደመጠበት ሁኔታ ፍርድ ቤት የዓቃቤ ህግን እግድ እንዳጸደቀው ነው የገለጸላቸው።
ይህ ውሳኔ ቢተላለፍም፤ አዘጋጆቹ የጋዜጣዋን ህትመት በመጪው ሳምንት ለማስቀጠል እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
ጋዜጠኛ ተመስገን፦”በፍርድ ቤቱ ውሳኔ አንስማማም!” በሚል ርዕስ ዛሬ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ባሰፈረው አጭር ማስታወሻ፦”በትላንትናው ዕለት የፍትህ ጋዜጣን እግድ እንዲያፀድቅ በዓቃቢ ህግ የቀረበለት ፍርድ ቤት ዕግዱን ተቀብሎ አፅድቆታል፡፡ ይህን ውሳኔ መቼም ቢሆን ተስማምቶ መቀበሉ፤ በህሊናችን ያለውን እውነተኛነት መካድ ስለሚሆንብን፤ ተስማምተን አንቀበለውም”ብሏል።
” በዚህ አይነቱ የአፈና እርምጃ በመደናገጥ የፍትህ ወጥ አቋም እንደማይቀየርም ለፍትህ ቤተሰቦች አረጋግጥላችኋለሁ”ያለው ተመስገን፤ ፍርድ ቤቱ ጋዜጣዋ የታገደችብትን ምክንያት በደብዳቤ ነገ እንደሚገልፅልን ስለነገረን፣ ደብዳቤው እንደደረሰን እዚሁ እለጥፍላችኋለሁ” በማለት ለፌስ ቡክ ጓደኞቹ ነግሯቸዋል።
ይህ ዜና እስከሚጠናቀርበት ጊዜ ድረስ በዚህ የተመስገን ማስታወሻ ስር ከ 60 በላይ ሰዎች አስተያዬት የሰጡ ሲሆን፤ ሁሉም የፍርድ ቤቱ ውሳኔ መርዶ እንደሆነባቸው ነው የገለፁት።
ከአስተያዬት ሰጭዎቹ መካከል መሰረት ፅጌ የተባለች ወጣት፦”ለማን ይጮኻል? ምን ዓይነት ጭቆና ነው!” ስትል፤ታሪኩ ታደሰ የተባለ ወጣት ደግሞ፦”ተመስገን ትግልህን እንዳታቆም! እውነት ሁልጊዜም አሸናፊ ናትና” ብሏል።
_____________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide