የፍርሃት ስሜት፣ ሁከት፣ አመጽ እንዲፈጠር የሚያነሳሳ ጽሁፍና የተንቀሳቃሽ ምስልን አሰራጭቶ የተገኘ ሰው በህግ የሚያስቀጣ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

ኢሳት (ሚያዚያ 5 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ በአገልግሎት ላይ ያሉ የተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮችን ለመመዝገብ በዝግጅት ላይ የሚገኘው መንግስት አመጽ የሚያነሳሳ ወይም ጹሁፍን ማስተላለፍን ጨምሮ ሌሎች ድርጊቶችን በህግ የሚያስቀጣ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ አቀረበ።

ይኸው በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው ረቂቅ አዋጅ ማንኛውም ሰው በህበረተሰቡ መካከል የፍርሃት ስሜት፣ ሁከት፣ አመጽ እንዲፈጠር የሚያነሳሳ ጽሁፍና የተንቀሳቃሽ ምስልን አሰራጭቶ ከተገኘ በህግ እንደሚቀጣ አመልክቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ማንኛውም ሰው ምርትን ወይንም አገልግሎትን ለማስተዋወቅ ወይም ለሽያጭ ለማቅረብ መልዕክቶችን በአንድ ጊዜ ወደ በርካታ ኢሜይል አድራሻዎች ያሰራጨ ከሆነ እስከ ሶስት አመት የሚደርስ የእስር ቅጣት እንደሚተላለፍበትም በአንቀጽ ማስቀመጡን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ከግለሰቦች ተግባር ጎን ለጎን በወታደራዊ ወይ ለአለም አቀፍ ግንኙነት ሲባል በተሰየመ የኮምፒውተር ዳታ ላይ የወንጀል ጥፋት የፈጸሙ አካላትም ከ15 እስከ 25 አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጡ በረቂቅ አዋጅ ሰፍሯል።

የተለያዩ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች መንግስት የመረጃ ዝውውርን ለመቆጣጠር ተግባራዊ እያደረገ ያለው ህግና ደንብ በሃገሪቱ ያለው አፈና ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ በመግለጽ ላይ ናቸው።

በስልጣን ላይ ያለው ገዢው የኢህአዴግ መንግስት የረቀቁ የኢንተርኔት የስለላ ድርጊቶችን ለመፈጸም ከአንድ የጣልያን የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጋር ውልን በማድረግ የስለላ ተግባር ሲፈጽም መቆየቱ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

ይህንንም ተከትሎ በሃገሪቱ የሚገኙ የእጅ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ለመመዝገብ ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን በአገልግሎቱ ላይ የበለጠ ቁጥጥርን ለማድረገም ረቂቅ አዋጅ መቅረቡን ለመረዳት ተችሏል።

የሂውማን ራይትስ ዎች ባለስልጣናት መንግስት እያካሄደ ያለው ቁጥጥር ቀድሞ የተተነበየ እንደነበርና አፈናው ወደ አሳሳቢ ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን ገልጸዋል።

ሃገሪቱ ካላት የህዝብ ቁጥር አንጻር የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች በአፍሪካ ደረጃም አነስተኛ የሚባል ቢሆንም መንግስት በአገልግሎቱ ላይ የሚያደገው ቁጥጥርና ክፍያ ከሌሎች ሃገራት የበለጠ መሆኑን የተለያዩ አካላት ያስረዳሉ።