ኢሳት ( ጥር 10 ፥ 2008)
የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከቀረበባቸው የሽብርተኛ ወንጀል ክስ ነጻ ተሰናብተው ጉዳያቸው በይግባኝ በመታየት ላይ ባሉ አምስት የፓርቲ አመራሮች ላይ ሊሰጥ የነበረን ብይን ለሁለተኛ ጊዜ አራዘመ።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ አቃቤ ህግ ከብሄራዊ ደህንነት ተገኝቷል የተባለ ማስረጃ “ኦሮጂናሉ” እንዲቀርብ ሲል ማክሰኞ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ፍርድ ቤቱ ባለፈው ቀጠሮው “የምንመረምረው ነገር አለ” በማለት በቀረበው ይግባኝ ላይ ሊሰጥ የነበረውን ብይን ለማክሰኞ ጥር 2008 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል።
ይሁንና፣ ብይኑን ይሰጣል የተባለው ፍርድ ቤቱ በአቃቢ ህግ በቀረበው ማስረጃዎች ላይ ያልተሟሉ ነገሮች እንዲቀርቡ በማለት በድጋሚ ተለዋጭ ቀጠሮን ለጥር 24, 2008 ሰጥቷል።
በአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ ሃብታሙ አያሌውን ጨምሮ በመኢአድና በአረና ፓርቲዎች ውስጥ በአመራርነት ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ ዳንዔል ሺበሺ፣ መምህር አብርሃ ደስታና አቶ አብርሃም ሰለሞ ከቀረበባቸው ክስ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ነጻ መሰናበታቸው ይታወሳል።
ይሁንና ከሳሽ አቃቤ ህግ የተሰጠው ፍርድ ተገቢ አይደለም በማለት ክሱ ዳግም እንዲታይለት ይግባኙን ለጠቅላላ ፍርድ ቤት አቅርቦ በማክሰኞው የፍርድ ቤት ውሎም አቃቤ ህግ በከፍተኛው ፍርድ ቤት አልተመረመረልኝም ያለው ማስረጃ ኦርጂናሉ ይቅረብ ሲል ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን፣ ከስልክም ሆን ከኢሜይል ተገኘባቸው የተባለው ማስረጃ ቃል በቃል ይቅረብ ሲል ጠይቋል።
የከፍተኛው ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ያቀረበው ማስረጃ የተሟላና በቂ አይደለም በማለት ተከሳሾች ራሳቸውን መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ ይሰናበቱ ሲሉ ከወራት በፊት ውሳኔ መስጠቱ የሚታወስ ነው።