ኢሳት (ግንቦት 22 ፥ 2009)
የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደሩትን 3.5 ሚሊዮን ዶላር ወደ ዱባይ አሸሽተዋል ከተባሉ ሁለት ተከሳሾች መካከል ትውልደ ግብጻዊና የአሜሪካ ዜግነት ያላቸውን ግለሰብ በ25 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ማክሰኞ ወሰነ።
ሁለተኛ ተከሳሽና በትውልድ ደቡብ አፍሪካዊ ሆነው የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ግለሰብ ደግሞ የመከላከያ ምስክር እንዲያቀርቡ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው አይመን አብዱል ሞትሊን ከተላለፈባቸው 25 አመት ጽኑ እስራት በተጨማሪ 252ሺ ብር እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል።
ሁለቱ ተከሳሾች ከ2003 እስከ 2005 አም ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኘው ስታር ፓይፕ በተባለ ሃገር በቀል ኩባንያ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተለያዩ ማሽነሪዎች ማስመጫ በሚል ገንዘብ መበደራቸውን ከሳሽ አቃቤ ህግ በክሱ አቅርቧል።
ተከሳሹ የተበደሩትን 3.5 ሚሊዮን ዶላር ወደ ዱባይ በማሸሽና በራሳቸው የሂሳብ አካውን በማስገባት ሃሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት አገልግሎት የማይሰጡ በርካታ ማሽነሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ አስገብተዋል ሲል አቃቤ ህግ በክሱ ዘርዝሯል።
ይሁንና ሁለቱ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ተከሳሾች ወንጀሉን እንዳልፈጸሙ በማስረዳት ክርክር ሲያካሄዱ መቆየታቸውን ለመረዳት ተችሏል።
ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ተከሳሹ አይመን አብደል ሞትሊን ላይ የመጨረሻ ፍርድ የሰጠ ሲሆን፣ የአንደኛው ተከሳሽ ማይክል ማሰን ላይ ምስክርነት እንዲያቀርቡ ባዘዘው ውሳኔ ላይ ለግንቦት 25, 2009 አም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶኣል።
የተላለፈው ፍርድ በተመለከተ የአሜሪካ መንግስት እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የለም።