ኢሳት (የካቲት 10 ፥ 2009)
የፌዴራሉ ከሳሽ አቃቤ ህግ የሽብርተኛ ክስ በተመሰረተባቸው አቶ በቀለ ገርባ ላይ የሰው ምስክር ማቅረብ ባለመቻሉ ተከሳሽ ኢሳትን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ያደረጓቸውን ንግግር በማስረጃነት ማስደመጥ ጀመረ።
አቃቤ ህግ ተከሳሽ አመፅን የሚያነሳሱ ንግግር አድርገዋል ብሎ በቀረበው በዚሁ ማስረጃ በተቃራኒው ተከሳሽ ከአመጽ የጸዳ (ጸረ-አመፅ) ትግል እንዴት መካሄድ እንዳለበት ሲናገሩ በቪዲዮው መደመጡ ታውቋል።
አቃቤ ህግ የአቶ በቀለ ገርባ ንግግር በይዘቱ ሁከትን የሚያነሳሳ ነው ሲል ለችሎት ቢያስረዳም የአቶ በቀለ ገርባ አንደኛ ጠበቅ ማህበሩ ምን እንደሆነ ቢጠይቁ አቃቤ ህግ አላቅም የሚል ምላሽ መስጠቱን ለመረዳት ተችሏል።
ለፍርድ ቤቱ አርብ ከቀረቡት የቪዲዮ ማስረጃዎች መካከል አቶ በቀለ ገርባ እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2015 አም መጨረሻ ላይ ከኢሳት ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ ለምስክርነት ቀርቧል።
ከሳሽ አቃቤ ህግ ተከሳሽ የሰጡት ቃለ-ምልልስ በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ካለው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር ግንኙነት እንዳለው ለችሎቱ አስረድቷል።
የቪዲዮ ማስረጃውቾን እያቀረበ ያለው አቃቤ ህግ በቀጣይ ቀጠሮው ተከሳሽ ከኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር ያደረጉትን ቃለምልልስ እንደሚያቀርብ ለፍ/ቤቱ ገልጿል።
አቶ በቀለ ገርባ ባለፈው አምት ሚያዚያ ወር በድጋሚ በቁጥጥር ስር በዋሉ ጊዜ ሌሎች 21 የሚሆኑ የኦሮሚ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) አመራሮችና አባላት በተመሳሳይ ሁኔታ ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።
ከሳሽ አቃቤ ህግ በሌሎች ተከሳሾች ላይ የሰው ምስክርን ጭምር በማቅረብ ክሱን ለማሳመን ቢጥርም በአቶ በቀለ ገርባ ላይ ግን እስካሁን ድረስ የሰው ምስክር ማረብ ሳይችል መቅረቱን አዲስ ስታንዳርድ መሄት በዘገባው አመልክቷል።
ለእስር የተዳረጉ የኦፌኮ አመራሮችና አባላት በህገወጥ መንግስት በሽብርተናኘት ከተፈረጀው የሮሞኦ ነጻነት ግንባት (ኦነግ) ጋር አባል እንደሆኑን ሁከትና አመጽን ለማካሄድ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ እንደነበር በክሱ ቀርቧል።
ፍርድ ቤቱ የቀሩ የአቃቤ ህግ ማስረጃዎችን ለመስማት ከፊታችን ሰኞ ተለዋጭ ቀጠን የሰጠ ሲሆን፣ አቃቤ ህግ በተከሳሽ አብደታ ነጋሳና በየነ ሩዳ ላይ የቪዲዮ ማስረጃዎችን እንደሚያቀርቡ ለችሎቱ ገልጿል።
በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ የኦፌኮ አመራሮችና አባላት እንዲሁም ደጋፊዎች ለእስር መዳረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በዚሁ አንድ አመት ያህል ጊዜ በዘለቀው ተቃውሞ ከ700 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።