ኢሳት (የካቲት 30 ፥ 2009)
የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶ/ር መረራ ጉዲና የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ባቀረቡት ጥያቄ ላይ ሃሙስ ተቃውሞን አቀረበ።
ዶ/ር መረራ ያቀረቡትን የዋስትና መብት ለመመልከት ተሰይሞ የነበረው ችግሎትም ከአቃቤ ህግ የቀረበለትን ተቃውሞ ተከትሎ ውሳኔውን ለአርብ በተለዋጭ ቀጠሮ ማራዘሙ ታውቋል።
ለፍትድ ቤቱ የባለ ሁለት ገፅ የተቃውሞ ደብዳቤን ያቀረበው አቃቤ ህግ ተከሳሽ የቀረበባቸው ክስ ከባድ እና ተደራራቢ ክሶc ባለፈው ሳምንት እንደተመሰረተባቸው ይታወሳል። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) አመራሩ በአውሮፓ ፓርላማ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለው በቤልጅየም በነበራቸው ቆይታ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በመወያየት ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተላልፈዋል ሲሉ ከሳሽ አቃቤ ህግ በክሱ አስፍሯል።
ከዶ/ር መረራ ጉዲና በተጨማሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋና የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ሃላፊ አቶ ጀዋር መሃመድ ተመሳሳይ ክስ እንደቀረበባቸው ይታወሳል።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ተከሳሾች ህገመንግስቱ በሃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል በማለት በአራት ክፍሎች ባቀረበው የክስ ቻርጁ አቅርቧል። በብቸኝነት ፍርድ ቤት በአካል በመቅረብ ክሳቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት ዶ/ር መረራ ጉዲና የቀረበባቸውን የወንጀል ክስ እንዳልፈጸሙ በመግለጽ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጥያቄን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
ይሁንና ሃሙስ የጽሁፍ ተቃውሞን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረበው ከሳሽ አቃቤ ህግ ተከሳሽ የዋስትና መብታቸው ቢጠበቅ ሊሰወሩ ይችላሉ ሲልም ስጋቱን ገልጿል።
በተከሻሱ ላይ የቀረበው ሶስት ተደራራቢ የህግ ድንጋጌዎች በመተላለፍ የቀረበ ክስ በመሆኑ ከቀረበው የወንጀሉ ከባድ መሆን ጋር ተገናዝቦ የቀረበው ዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ብይን እንዲሰጥልን በማከበር እናመለክታለን ሲል ከሳሽ በጽሁፉ አመልክቷል።
የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ያቀረበውን መቃወሚያ በመመርመር ዶ/ር መረራ ጉዲና በቀረቡት የዋስትና መብት ጥያቄ ላይ አርብ ብይን ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።