የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት አቶ ሃብታሙ አያሌው በሃኪሞች ቦርድ ከሃገር ውጭ እንዲታከም የታዘዘን ውሳኔ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲያጣራ አዘዘ

ኢሳት (ነሃሴ 2 ፥ 2008)

የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጽኑ በህመም ላይ የሚገኘው አቶ ሃብታሙ አያሌው በሃኪሞች ቦርድ ከሃገር ውጭ እንዲታከም የታዘዘን ውሳኔ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መርምሮ እንዲያጣረ አዘዘ።

ፍርድ ቤቱ ከዚህ ቀደም ከሃገር እንዳይወጣ እገዳ ተጥሎበት የሚገኘውን የአንድነት ፓርቲ አመራሩ አቶ ሃብታሙ አያሌው ያቀረበውን የሃኪም ማስረጃ የተሟላ አይደለም ሲል የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የአቶ ሃብታሙ አያሌው ቤተሰቦች በሶስት ስፔሻሊስት ሃኪሞች የተደገፈን የህክምና ቦርድ ለፍርድ ቤት ያቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱ የሃኪሞች ቦርድ ያቀረቡትን ውሳኔ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ማጣራትና ምርመራ እንዲካሄድበት ወስኗል።

የህክምና ቦርድ አቶ ሃብታሙ አያሌው በውጭ ሃገር ህክምና እንዲያገኙ ውሳኔን ቢሰጡም ፍርድ ቤቱ አቶ ሃብታሙ ህመሙ በአገር ውስጥ ማከም መቻል አለመቻሉን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲያጣራ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ በሃኪሞች ውሳኔ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለምን ምርመራና ማጣራትን እንዲያካሄድ ማዘዙን በተመለከተ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ ትዕዛዙ ከተለመደው አካሄድ ውጭ መሆኑን የተለያዩ አካላት አስረድተዋል።

ፍርድ ቤቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚሰጠውን ሪፖርት ለመቀበልና በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ለመስከረም 25, 2009 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮን ሰጥቷል።

አቶ ሃብታሙ አያሌው ከሌሎች የፓርቲ አመራሮች ጋር ቀርቦበት በነበረ የሽብርተኛ ወንጀል ክስ መከላከል ሳይስፈልገው በነጻ እንዲሰናበት በታችኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ቢሰጠውም ከሳሽ አቃቤ ህግ ውሳኔውን ባለመቀበል ይግባኝን አቅርቦ ይገኛል።

ይሁንና ተከሳሹ በእስር ቤት ቆይታው ወቅት በተፈጸመበት ኢሰብዓዊ ድርጊት በህመም ሊዳረግ መቻሉን አምነስቲ ኢንተርናሽናልና የአቶ ሃብታሙ የቅርብ ጓደኞች ሲገልፁ መቆየታቸው ይታወሳል።