የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት 20 ተከሳሾችን በቀረበባቸው የሽብርተኛ ወንጀል ክስ ጥፋተኛ ናቸው ሲል ብይን አስተላለፈ

ኢሳት (ታህሳስ 12 ፥ 2009)

የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሁለት ጋዜጠኞችን ጨምሮ 20 ተከሳሾችን በቀረበባቸው የሽብርተኛ ወንጀል ክስ ጥፋተኛ ናቸው ሲል ረቡዕ ብይን አስተላለፈ።

የጥፋተኝነት ብይኑን የሰጠው ፍርድ ቤቱ በእነ ከድር ሞሃመድ የሱፍ ክስ መዝገብ የተለያዩ ክሶች ቀርቦባቸው በነበሩት ተከሳሾች ላይ የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔን ለመስጠት ለቀጣዩ ሳምንት ቀጠሮ መያዙ ታውቋል።

ከሁለት አመት በፊት ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩት ተከሳሾች የሙስሊም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን ከእስር ቤት ለማስለቀቅ እንዲሁም የሽብር ድርጊቶችን ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል የሚል የክስ ቻርጅ ቀርቦባቸው እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።

የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ባለፈው አመት ከሙስሊሙ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ጋር ለእስር ከተዳረጉት መካከል በዘጠኙ ላይ የረዥም ጊዜ የእስር ቅጣት አስተላልፎ እንደነበር የሚታወስ ነው።

የቀሩት ዘጠኝ ተከሳሾች ደግሞ በፕሬዚደንት ሙላቱ ተሾመ ይቅርታ ተደርጎላቸዋል ተብለው ከእስር በነጻ መሰናበታቸው በወቅቱ ተዘግቧል።

ረቡዕ የጥፋተኝነት ብይን ከተላለፈባቸው መካከል ጋዜጠኛ ካሊድ ሞሃመድ እና ዳርሴማ ሶሪ እንደሚገኙበትም ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

ተከሳሾቹ በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች የተለያዩ ጹሁፎችን በማሰራጨት መንግስት የኮሚቴ አባላትን አስሯል የሚሉ መረጃዎችን በማሰራጨት ሁከት ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል ተብለዋል።

የሙስሊሙ ማህበረሰብ መንግስት በሃይማኖታችን ጣልቃ ገብቷል በማለት አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች ከአራት አመት በላይ ሁለገብ የሆነ ተቃውሞን ሲካሄዱ መቆየታቸው ይታወሳል።