ኢሳት (ግንቦት 8 ፥ 2009)
የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ዮናታን ተስፋዬ ላይ በተመሰረተበት የሽብርተኛ ክስ የጥፋተኝነት ብይን ማክስኞ ሰጠ።
በተለያዩ የማህበራዊ ድረገጾች በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ዙሪያ ጽሁፎችን ሲያቀርብ የነበረው ዮናታን በኦሮሚያ ክልል ከተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ከአመት በፊት ለእስር መዳረጉ ይታወሳል።
በግንቦት ወር 2008 አም ክሱን የመሰረተው ከሳሽ አቃቤ ህግ ተከሳሹ በማህበራዊ ድረገጾች አመፅ እንዲስፋፋ ቅስቀሳን አድርጓል በሚል የሽብርተኛ ወንጀል ክስ መስርቷል።
ይሁንና በከሳሽ አቃቤ ህግ የቀረበበትን ክስ በመቃወም ዮናታን ተስፋዬ ዶ/ር መረራ ጉዲናን አቶ በቀለ ገርባንና ሌሎች አካላትን በምስክርነት በማቅረብ ማስደመጡን ለመረዳት ተችሏል።
በጉዳዩ ዙሪያ የግራ ቀኝ ክርክርን አዳምጦ ማክሰኞ ብይን የሰጠው ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን በቀረበበት የሽብርተኛ ወንጀል ክስ ጥፋተኛ በማለት ብይን መስጠቱን አዲስ ስታንዳርድ ጋዜጣ ዘግቧል።
ዮናታን ተስፋዬ በከሳሽ አቃቤ ህግ የቀረበበትን ክስ ለመከላከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንዲሁም ዶ/ር ያቆብ ሃይለማሪያምን በምስክርነት አቅርቦ እንደነበርም የሚታወስ ነው።
ይሁንና የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በምስክርነት ሲያደምጥ የቆየውን የመከላከያ ማስረጃ ውድቅ በማድረግ ተከሳሹ ላይ የጥፋተኝነት ብይን አስተላልፏል።
የተከሳሽ ጠበቃ የሆኑት አቶ ሽብሩ በለጠ የተሰጠውን ብይን በመቃወም ጉዳዩ በወንጀለኛ ክስ እንዲታይ ይግባኝ እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል።
የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በተከሳሹ ላይ የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔን ለመስጠት ለግንቦት 17 ፥ 2009 አም ቀጠሮ የያዘ ሲሆን፣ የሽብርተኛ ወንጀሉ እስከ 20 አመት ድረስ በእስር ሊያስቀጣ እንደሚችል የህግ አካላት ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የፖለቲካ አመራሮችና አባላትን ጨምሮ ከ24 ሺ በላይ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ወደ 5ሺ አካባቢ የሚጠጉት ክስ ይመሰርትባቸዋል ተብሏል።
ሂውማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የኢትዮጵያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መስፋፋቱን ሲገልፅ ቆይተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመውን ግድያና የጅምላ እስራት በገለልተኛነት ለመመርመር ጥያቄን ቢያቀርብም መንግስት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።
መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አካሄጀዋለሁ ባለው ምርመራው 669 ሰዎች መሞታቸውን ለፓርላማ ማቅረቡ ይታወሳል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በበኩላቸው ሪፖርቱን እንደማይቀበሉት በመግለጽ ድርጊቱ በገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲካሄድበት ጥሪን እያቀረቡ ይገኛሉ።
በጥቅምት ወር ተግባራዊ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከ ፊታችን ነሃሴ ወር ድረስ ቀጣይ እንዲሆን ተወስኗል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፣ የዮናታን ተስፋዬ ጠበቃ አቶ ሽብሩ በለጠ ፍርድ ቤቱ በደንበኛቸው ላይ የሰጠው ብይን ሌሎች ሰዎች ሃሳባቸውን በነጻነት እንዳይገልፅ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ገልጸዋል።
ደንበኛቸው በማህበራዊ ድረገፅ በተለይ በፌስ ቡክ ላይ ባሰፈራቸው ጽሁፎቹ በሽብርተኛ ወንጀል ክስ ተመስርቶበት ጥፋተኛ መባሉ አግባብ እንዳልሆነም አክለው አስረድተዋል።