የፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ብቃቴ አድጓል አለ

ጥቅምት ፲፩(አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የፌዴራል ፖሊስ በ2006 በጀት ዓመት በ36 መዝገቦች በኦነግ፣ በግንቦት ሰባት፣ በኦብነግ፣ በጋህነን፣ በቤህነን እንዲሁም በአልሻባብ ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎችን መክሰሱን በመጥቀስ የፌደራል ፖሊስ ሽብርን የመከላከል አቅሙ እንዳደገ በመግለጽ ራሱን አሞካሽቷል፡፡

ፌዴራል ፖሊስ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ ባለፈው ዓመት 36 የሽብር መዝገቦች መካከል በ27 ቱ ላይ ምርመራ ተጠናቆ ለሚመለከተው ክፍል መመራቱን አስታውቆአል፡፡ ከነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከል 4 የኦነግ፣ 6 የግንቦት ሰባት፣ 1 ኦብነግ፣ 3 ጋህነን፣ 2 ቤህነን ኢንዲሁም 2 የአልሻባብ አባላት ናቸው ብሎአል፡፡

እነዚህ ተጠርጣሪዎች በኤርትራ መንግስት የሰለጠኑና የተሰማሩ ናቸው ሲል አክሏል። ፖሊስ ባለፈው    ዓመት ብቻ በሽብርተኝነት የተጠረጠሩ 119 ተከሳሾች ጥፋተኛ ተብለው ከ1 እስከ 25 ዓመት እንደተፈረደባቸው ጠቅሶ ይህም ፖሊስ የተፋጠነ ፍትህ የማስገኘትና የማስቀጣት አቅሙ የጨመረ መሆኑን ያሳያል ብሎአል፡፡

በሌላ በኩል ሰሞኑን በሸኮ መዠንገር ላይ በፌደራል ፖሊስ ላይ ስለደረሰው ከፍተኛ ጉዳት መስሪያ ቤቱ ምንም ለማለት አልፈለገም።

የፌደራል ፖሊስ ሽብርን የመከላከል አቅሜ አድጓል ቢልም፣ አለማቀፍ ውግዘት ባልተለየው የጸረ ሽብር አዋጅ አማካኝነት ጸሃፊዎችን፣ ጋዜጠኞችንና ፖለቲከኞችን ከተጠቀሱት ድርጅቶች ጋር ያብራሉ በማለት ይከሳል በሚል ተደጋጋሚ ውግዘት ሲድርስበት ቆይቷል።