ግንቦት ፳፭(ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በአምስት አመት እቅዱ ላይ መስሪያ ቤቱን የሚለቁ ወታደሮች መበራከታቸውን እና አዳዲስ አባላትን ለማሰልጠን የተደረገው ጥረትም አለመሳካቱን ገልጿል። መስሪያ ቤቱ ባዘጋጀው ዝርዝር ሪፖርት ላይ ለፍልሰቱ የሰጠው ምክንያት ኢኮኖሚያዊና የአቋም መላላት የሚል ነው። በሃገራችን ይላል ሰነዱ “ ካለው አጠቃላይ እድገት የሚመነጭ የስራ አማራጭ በማየትና አንዳንድ የአላማ ጽናት የሚጎድላቸው አባላትም በኩብለላም ሆነ ህጋዊ የስንብት ጥያቄ በማቅረብ የሚለቁ አባሎች ስላሉ ፍልሰቱን ሙሉ በሙሉ ማስቆም ባለመቻሉ የሰላም ሰራዊት ግንባታ ትግበራ እንደተጠበቀ ሆኖ የሰራዊቱን የኑሮ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለማሻሻል የሚያግዙ ድጋፎች ያስፈልጋሉ ።”
“በየጊዜው በተቋሙ የሚታየው የሰው ሀይል ፍልሰትና አዳዲስ የሰው ሀይል ተቋሙ ለመሳብና ለማቆየት ያለው ሁኔታ ምቹ አለመሆን” ስጋት ፈጥሮብናል የሚለው ፌደራል ፖሊስ፣ ከኢኮኖሚና ከኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን እድገት ጋር ተያይዞ የወንጀል አፈጻጸሞች እየከበዱና እየተራቀቁ መምጣታቸው የህግ ማስከበር ስራውን አክብዶታል ብሎአል። ሐይማኖትን እንደ ሽፋን የሚጠቀሙ አክራሪ ቡድኖች እንቅስቃሴ በየጊዜው በአለም ላይ እየተበራከተ መምጣቱና ተለዋዋጭ የሽብር ዜዴዎችን የመተግበር ሁኔታቸው እያደገ መምጣት፤ አንዳንድ ቡድኖች የሀገራችንን የብሔር ብሔረሰቦች ልዩነት እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ግጭት በመፍጠር ድብቅና አፍራሽ የፖለቲካ አላማቸውን ለመተግበር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፤ በሰላማዊ መንገድ ተደራጅተውና ትክክለኛ ህዝባዊ አመለካከት ይዘው ለነጻ ምርጫ ለመወዳደር አቅም ያጡ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ህዝቡ ውስጥ ተሸሽገው ድብቅ አላማቸውን ለማሳካት ብጥብጥና ሁከት ለማስነሳት የሚሞክሩ መሆኑ፤ የሽብርተኝነት ወንጀል ለመፈጸም የሚያግዙ ሁኔታዎች እና ጂኦፖሊቲካል አካባቢ ውስጥ መኖራችን የህግ ማስከበርና ወንጀልን የመከላከል አላማችን ላይ ጫና እየፈጠረ ነው ሲል ይዘረዝራል።
የፈደራል ፖሊስ መደበኛ አባላት በአብዛኛውም የተቃዋሚ ደጋፊዎች መሆናቸው በተለይም በኢሳትና በፌስቡክ የሚለቀቁ መረጃዎችን በንቃት እንደሚከታተሉ ምንጮች ይገልጻሉ። የፌደራል ፖሊስ አመራሮች የሚፈጽሙትን ሙስና እና የሰራዊቱን ህይወት በተመለከተ ኢሳት በሚቀጥለው ሳምንት መግቢያ ላይ በሰነድ የተደገፈ ልዩ ሪፖርት እንደሚያቀርብ ለመግልጽ ይወዳል።