(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 9/2010) በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ የፌደራል የጸጥታ አካላት በአፋጣኝ ገብተው ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጥሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ትዕዛዝ ሰጡ።
ሁለቱም ክልሎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ መሰረት የጸጥታ አካላት እንዲገቡም ስምምነታቸውን መግለጻቸው ተመልክቷል።
ለመቶሺዎች መፈናቀል፣ ለብዙዎች ሞትና አካል መጉዳል ምክንያት የሆነው ግጭት ከአመት በላይ ዘላቂ መፍትሔ ሳያገኝ ቆይቷል።
ይህንን ሁኔታ በዘላቂነት ለመፍታት የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊቱ የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ስራ እንዲሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
ዛሬም ባረጀና ግዜው ባለፈበት ፋሽን ግጭቶች እየተከሰቱ የሰው ሕይወት እየጠፋ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ።
በተለይም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በሚያሳዝን ሁኔታ ይህው ሁኔታ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በዚህ ድርጊት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተሳተፉ ግለሰቦችና ቡድኖች በሕዝቦች መካከል ግጭትን ከሚፈጥሩና ከሚያባብሱ ድርጊቶቻቸው እንዲታቀቡም አሳስበዋል።
አክቲቪስቶችና አርቲስቶችም እንዲሁም በልዩ ልዩ ሙያ ላይ የሚገኙ ግለሰቦችና ቡድኖችም ከቆስቋሽ ድርጊቶች ይልቅ በሚያስማሙና በሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የሃገር መከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስም በየትኛውም አካባቢ ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት በሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ወገኖችን በበቂ መረጃና በጥበብ ለፍርድ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን መመሪያ ተከትሎ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳና የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳትን አቶ አብዲ መሃመድ ኢሌ በጉዳዩ ላይ መወያየታቸው ተመልክቷል።
ሁለቱም ርዕሰ መስተዳድሮች የፌደራል መንግስት የጸጥታ አካላት ገብተው የማረጋጋቱን ስራ እንዲሰሩ መስማማታቸውም ታውቋል።