(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 27/2010) በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ውስጥ በታራሚዎች ላይ ከሚደርሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ከኃላፊነታቸው ተነሱ ።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ አራት ምክትል ዳይሬክተሮች በአዳዲስ ተሿሚዎች ተተክተዋል።
የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት እንደሚጣስ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።
በህግ ቁጥጥር ስር ባሉ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከአካል ማጉደል እስከ ሕይወትን ማጣት የሚያደርሱ መሆኑንም ኢሳት በተደጋጋሚ ሲዘግብ መቆየቱ ይታወሳል።
ዛሬም በእስር ላይ ያሉና በቅርቡ ከእዚህ ስቃይ የወጡ ዜጎች የደረሰባቸውን በመናገርና በማሳየት እውነታውን ለህዝብ ይፋ አድርገዋል።
በቅርቡ በመገናኛ ብዙሃን የወጡት መረጃዎችም በማረሚያ ቤቶቹ ለሚደርሰው ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ትልቅ ማሳያ እንደሆኑም የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በተቋሙ ሲፈጸሙ የነበሩ ሌብነቶች፣የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የአሰራር ግድፈቶች ፣የሙያ ብቃት ማጣትና በታሳሪዎች መካከል የሚፈጸመው አድሎአዊት የእስር ቤቱ የከፋ ገጽታ መገለጫዎች እንደሆኑም ይነገራል።
በእስር ቤቶቹ ውስጥ በንጹሃን ዜጎች ላይ ይህን አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ የነበሩ ሃላፊዎችም ከስልጣናቸው እንዲነሱ ተደርገዋል።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ እንደሚሉት ከሆነም ተቋማዊ ለውጥ በማስፈለጉ አመራሮቹን በአዲስ መተካት ግድ ብሏል።
በዚህም መሰረት አቶ ጀማል አብሶ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል።
ረዳት ኮሚሽነር ያረጋል አደመ ደግሞ የአስተዳደሩ የፋይናንስና የሰው ሃብት ዘርፍ ኃላፊ ሲሆኑ ኮማንደር ሙላት አለሙ የጥበቃ እና አስተዳደር ዘርፍ ሀላፊ ተደርገዋል።
ኮማንደር ወንድሙ ጫማም በምክትል ዋና ዳይሬክተር የመሰረታዊ ዘርፍ ሃላፊ ሆነዋል።
ኮማንደር ደስታ አስመላሽ ደግሞ የተሃድሶ ልማት ዘርፍ ኃላፊነትን መረከባቸውን ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ አዲስ ተሿሚዎች ከዚህ በፊት በፌደራል ማረሚያ ቤቶቹ ውስጥ ሲፈጸሙ የነበሩትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ማረምና ከማህበረሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን መመለስ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ከስልጣን ላይ የተነሱት ሃላፊዎችም ጉዳይ ቢሆን ከዚህ በፊት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲሁም በሰብአዊ መብት ጥሰቱ ውስጥ የነበራቸውን ድርሻ በማጣራት ህግ ፊት እንዲቀርቡ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።