ሐምሌ ፳፮ ( ሀያ ስድስት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ወራትን ያስቆጠረው የኦሮሞ ህዝብ የመብት ጥያቄ የፈታችን ቅዳሜ በመላው ኦሮምያ አካባቢ እንደሚካሄድ ታውቋል። በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የኦሮሞ ህዝብ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ትግሉን ቢያካሂድም እያገኘ ያለው ምላሽ ግን በተቃራኒው ጥይት መሆኑ በርካታ ዜጎችን አስቆጥቷል።
በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ገዢው ፓርቲ የሚያካሂደውን ግድያ እንዲያቆም፣ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ አጋዚ ክልሉን ለቆ እንዲወጣ እና ሌሎችም ጥያቄዎች ይቀርባሉ።
በኦሮምያ እየተካሄደ ባለው ተቃውሞ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አልቀዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ታስረዋል። ባለፈው እሁድ በአወዳይ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ ከ11 በላይ ዜጎች ተገድለዋል። ከ25 በላይ ሰዎች ደግሞ ክፉኛ ቆስለዋል።