የፉጋ ማህበረሰብ እየተባሉ የሚጠሩት ለመጥፋት ተቃርበዋል ተባለ

ታኅሣሥ ፲፯ (አሥራ ሠባት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በደቡብ ክልል በአላባ ልዩ ዞን የሚገኝው የፉጋ ማህበረሰብ ከፍተኛ ለሆነ መገለል እና መድሎ ተጋላጭ በመሆኑ እና ምንም አይነት ፤ የትምህርት ፣ የጤና ተደራሽነት በማጣቱ ወደ ማህበረሰባዊ በቀል እና ጥላቻ የወለደው አመፅ ሊያመሩ እንደሚችሉ የፌደሬሽን ምክርቤት አስታወቀ፡፡

ምክር ቤቱ ባስጠናው ጥናት  ኢህአዴግ እስካሁን ድረስ አገዛዙን ከተቆጣጠረበት ጊዜ አንስቶ ማህበረሰቡ “የተካደ የተናቀ እና የተገፋ ሰውነቱን ይዞ ከዜጎች ተነጥሎ እየኖረ ነው” ብሏል፡፡ እነዚህ በከምባታ ዞን ዱራሜ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች፣  ከሌላው ኅብረተብ ተነጥለው ኑሮ መስርተው የሚገኙ ሲሆን ወደ ቤታቸው ለመድረስ ረዥም የእግር መንገድ መጓዝ፣ የመቃብር ሥፍራ እንዲሁም ደን ማቋረጥ ግድ ይላል፡፡ እነዚህ የተገለሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች  ‹‹ፉጋ›› የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ሲሆን፣ ስያሜው አሉታዊ ትርጉም የያዘ ቢሆንም፣  አሁንም ድረስ የፊደሬሽን ምክርቤት እና የክልሉ ምክርቤት የውርደት ስማቸው ን አፅድቆ በፊደራል ሳይቀር መዝግቧቸው ይገኛሉ፡፡

በሸክላ ስራቸው የሚታወቁት ፉጋዎች፣ በሌሎቹ የአካባቢው ተወላጆች ዘንድ ከሰው በታች ተደርገው ይታያሉ፡፡ ቁጥራቸው በአሁኑ ወቅት ከ82 እስከ 95 ሺሕ እንደሚደርስ ይገመታል የሚለው ጥናቱ፣  የሚኖሩበት የተወሰነ ቦታ የሌላቸው እና አንዳቸው ቤት ሰርተው የመሬት ባለቤት ሁነው መኖር ያልቻሉ እና የመሬት ባለቤትነታቸው እንኳን ያልተረጋገጠላቸው ጎስቋላ ዜጎች ናቸው ይላል፡፡ ፉጋዎች መሬታቸውን በየጊዜው እየተነጠቁ ብዙ ጊዜም በጫካ ውስጥ አልያም ከሌሎች መሬት ተጠግተው ይኖራሉ።በየጊዜው ከቦታቸው ስለሚፈናቀሉም  ሸክላ የሚሠሩበትን አፈር ለማግኘትም እየተቸገሩ ህልውናቸው አደጋ ውስጥ ወድቋል።

በአካባቢያቸው ያሉ ሌሎች ብሄሮች ለፉጋዎች ምንም ዓይነት ክፍያ ሳይከፍሉ የተለያዩ ሥራዎችን ያሠሯቸዋል፡፡ የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ አሜን ብለው ካልተቀበሉ ከሚኖሩበት ይፈናቀላሉ፡፡ ስለዚህም የሚታዘዙትን የጉልበት ሥራ ለመሥራት ይገደዳሉ፡፡ከእነዚህ  ጋር ማኅበራዊ መስተጋብር መፍጠር እንደማይቻል የሚጠቁመው ጥናቱ ፣ድንገት መንገድ ላይ ሌላ የሌላ ብሄር ተወላጅ ቢያገኙ እንኳን ከርቀት ክብርን በሚያጎላ መልኩ እየሰገዱ ሰላምታ ማቅረብ ግዴታቸው ነው፡፡በሠርግ፣ በለቅሶና በሌሎችም ማኅበራዊ ጉዳዮች ከሌሎች  ጋር እኩል መቀመጥ አይችሉም፡፡ በረንዳ ላይ ከአንደኛው ጥግ ትራፊ ምግቦችን እንዲመገቡ ይደረጋሉ። ሌሎች በሚጠጡበት ዕቃዎች እንዲጠጡም አይፈቀድላቸውም፡፡ በመሆኑም ውኃም ይሁን ሌሎች  ነገርሮች በቅጠል እንዲጠጡ ይገደዳሉ፡፡ የሚያስፈልጋቸውን ወጥተው ለመሸመት ቢሹ እንኳ ሻጩ ከእጃቸው ገንዘብ መቀበል ስለማይፈልግ ይቸገራሉ፡፡ የሕዝብ ትራንስፖርት መጠቀምም አይችሉም፡፡ አንገታቸው ላይ ጣል ከሚያደርጉት የበግ ቆዳ ውጪ አልባስ መጠቀምም አይፈቀድላቸውም፡፡

በደቡብ ክልል በዳውሮና በቦንጋ አካባቢ የሚገኘው ‹‹መንጃ›› የተባለው የኅብረተሰብ ክፍልም ተመሳሳይ መገለል ይደርስበታል፡፡ መንጃዎች እንደ ፉጋዎች ሁሉ ከሌላው ማኅበረሰብ ተነጥለው በጫካ ዙሪያ ይኖራሉ፡፡ ብዙ ጊዜም አድነው የሚመገቡ ሲሆን፣ ከሌላው የተገለሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በይበልጥ የተገፉ መሆናቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆነችው ወይዘሪት ማጂ ኃይለማርያም በጥናት አረጋግጣለች።

በዳውሮ አካባቢ ቁጥራቸው 11,000 የሚሆኑ መንጃዎች ነበሩ፡፡ የሚኖሩት ከኅብረተሰቡ ተነጥለው ከተራራ ጫፍ ላይ ወይም ከገደል ሥር ነው፡፡ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት አስከብሬአለሁ በማለት በያመቱ በቢሊዮን ብር ወጪ እያወጣ የብሄር ብሄረሰቦችን በአል የሚያከብረው ህወሃት/ኢህአዴግ፣ በደቡብ ክልል ህልውናቸው በችጋር ምክንያት እየጠፋ ያሉትን ማህበረሰቦች ለመታደግ ምንም ጥረት ሲያደርግ አይታይም። ይልቁንም የሰፈሩበት መሬትን ለልማት በሚል እየነጠቀ በየጊዜው ህልውናቸው አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ እያደረገ ነው።

በአገሪቱ ውስጥ ማንነታቸው ተርስቶና መሬታቸው ለልማት የፈለጋል በሚል ህልውናቸው አደጋ ውስጥ የወደቁ በርካታ ብሄረሰቦች መኖራቸውን ዘጋቢያችን በሪፖርቱ ጠቅሷል።