የፈደራል ፖሊስ አባላት ሁለት የአፋር ተወላጆችን ከክልሉ ፖሊስ እጅ ነጥቀው ገደሉ

ሰኔ ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የፈደራል ፖሊስ አባላት  ሁለት የአፋር ተወላጆችን ከክልሉ ፖሊስ እጅ ነጥቀው  ገደሉ የዱብቲ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ፤ የፌዴራሎቹን ድርጊት ተቃውመዋል።

የኢሳት  ወኪል ከስፍራው እንደዘገበው፤ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የተወከሉ ፖሊሶች በዱብቲ ወረዳ ፖሊስ ቁጥጥር ስር ይገኙ የነበሩ አፋሮችን በጉልበት በመውሰድ አንዱን መኪና ውስጥ ወዲያውኑ ሲረሽኑት፤ ሌላኛውን ደግሞ ቁስለኛ አድርገውታል።

ፌደራል ፖሊሶቹ  የሟቹን አስከሬን እና ቁስለኛውን በክልሉ ምክር ቤት ፊት ለፊት በትናንትናው እለት ጥለው ሄደዋል። ችግሩ፤ ከሶስት ወራት በፊት የተፈጸመውን ግድያ የተከተለ ነው።

ኢሳት አንድ የ17 አመት ወጣት በፌደራል ፖሊስ አባላት መገደሉን በዘገበ በሳምንታት ውስጥ፤  ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባላት እንደተገደሉ መዘገባችን ይታወሳል።

“ የፌደራል ፖሊስ አባላትን የገደሉት፤ የሟቹ ዘመዶች ናቸው” የሚል ግምት የያዘው የዱብቲ ወረዳ ፖሊስ ፣ 12 የሚሆኑ የሟቹን ቤተሰቦች በቁጥጥር ስር አውሎ ነበር።

ይሁንና የወረዳው ፖሊስ ጉዳዩን ለመጣራት ዝግጅት በሚያደርግበት ወቅት ነው በኢንስፔክተር አይናለም የተመራው የፌደራል ፖሊስ ቡድን- ተጠርጣሪ እስረኞችን ወስዶ የረሸናቸውና ቁስለኛ ያደረጋቸው።

ጉዳዩን በማስመልከት ኢሳት ያነጋገራቸው የዱብቲ ወረዳ ፖሊስ አዣዥ፤ < ድርጊቱ በየትኛውም የአፍሪካ አገር ያልታየ፣ በክልሉ ፖሊስ ላይ ህዝቡ አመኔታ እንዲያጣ የሚያደርግ ስራ መሆኑን በመጥቀስ፤ አውግዘውታል። ****

የአፋር ሰብአዊ መብቶች ድርጅት ሊ/ቀመንበር የሆኑት አቶ ገአስ አህመድ በበኩላቸው “ይህ  የሽፍታ መንግስት ድርጊት ነው” በማለት ነው ድርጊቱን አምርረው የኮነኑት።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide