ነሃሴ ፲፯ ( አሥራ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የቤት እንስሳትም እየሞቱ ነው
በምስራቅ ሸዋ ዞን የፈንታሌ ወረዳ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ባጋጠማቸው ድርቅ ሳቢያ ለከፍተኛ ስቃይ መዳረጋቸውን አስታወቁ። በፈንታሌ ሃሮ ሁባ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አቶ ቦራ ሮቡ ኢቱ ሁኔታውን ሲያስረዱ ”በድርቅ በተጠቃው ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ የሆንነው ሁሉ ልጆቻችንን መመገብ አለመቻላችን ያናድደናል። የከብቶቻችን ሁኔታው አሳሳቢ ነው። የቤት እንስሳቶች በድርቁ ክፉኛ ከስተዋል። ወተት መስጠት አይችሉም። ቢሸጡም ዋጋ አያወጡም። አብዛሃኞቹ እየሞቱብን ነው።” ብለዋል።
በእግራቸው በቀን ከሶስት ሰዓታት በላይ ውሃ ፍለጋ ሲማስኑ እንደሚውሉም ተናግረዋል። ልጆቻቸውም ትምህርት ቤት ከመሄድ ይልቅ ውሃ በማምጣት ቤተሰቦቻቸውን ስለሚያግዙ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ታዳጊ ሕጻናት መጻኢ እጣ ፈንታቸው አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ዩኒሴፍ አስታውቋል። ድርቁን ተከትሎ ነዋሪዎች የትውልድ ቀያቸውን በመተው መፍለስ ጀምረዋል። በተለይ በፈንታሌ ወረዳ አካባቢ ሕጻናት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል፣ ውሃ ፍለጋ በሚሄዱበት ወቅት ሴቶች የወሲብ ትንኮሳ ሰለባ እየሆኑ ነው።
በኢትዮጵያ ቁጥራቸው ከ6 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕጻናት በከፍተኛ ርሃብ፣ ሕመምና፣ የውሃ እጥረት መጋለጣቸውን ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ በጥናት ሪፖርቱ አመልክቷል።