የጸጥታ አካላት በጎንደር ህዝብ ላይ የሚያደርሱትን ግድያና አፈና በመቃወም በዋሽንግተን ዲሲ ሰልፍ ተደረገ

ኢሳት (ሃምሌ 11 ፥ 2008)

ባለፈው ሳምንት በጎንደር ከተማና አካባቢዋ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ሰላማዊ ጥያቄን ባቀረቡ ነዋሪዎች ላይ የወሰዱትን ግድያና እስራት በመቃወም ነዋሪነታቸው በዚህ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማና አካባቢዋ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ሰኞ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ኣካሄዱ።

የተለያዩ መፈክሮችን ሲያስተጋቡ ያረፈዱት ሰልፈኞች መንግስት የማንነት ጥያቄን እያቀረቡ ባሉ አካላት ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ የሚወገዝና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።

“ግድያ ይብቃ”  “ሰላም በኢትዮጵያ ይስፈን”፣ “ለነጻነታችን ማንኛውንም መስዋዕትነት እንከፍላለን”፣ “የወያኔ አጫፋሪዎች ሳይረፍድ ከህዝብ ጎን ቁሙ” የሚሉ መፈክሮችን ሲያስተጋቡ ያረፈዱት ሰልፈኞች የአሜሪካ መንግስት አምባገነን መሪዎችን ከመደገፍ እንዲታቀቡ ጠይቀዋል።

ዋሽንግተን ዲሲ ከተማና አካባቢዋ በሚገኘው ግብረ ሃይል በተጠራው በዚሁ ተቃውሞ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ከሜሪላንድ እና ቨርጂኒያ ግዛቶች የመጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሃገሪቱ በተለያዩ ክልሎች በመካሄድ ላይ ያለው ግድያና አፈና እንዲቆም በመጠየቅ ተቃውሞን አሰምተዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች በመፈጸም ላይ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚያሳዩ ምስሎችን ያነገቡ ሰልፈኞች ገዥው የኢህአዴግ መንግስት በሃገሪቱ እየፈጸመ ላለው ግድያ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠያቄ መሆኑን ገልጸዋል።

ዜጎች የሌላቸውን መንነት በሃይል እንዲቀበሉ ማድረጉ ችግርን ከማባባስ ውጭ የሚያመጣው መፍትሄ የለም ሲሉ በሰላማዊ ሰልፉ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስታውቀዋል።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና አክቲቪስቶች ንግግር አድርገዋል። የጎንደር ህብረትን በመወከል ንግግር ያደረጉት ፕሮፌሰር አንተአያል ገ/ስላሴ ለሰላማዊ ሰልፈኞቹ ሲናገሩ፣ ዕብሪተኛ የህወሃት መሪዎች  በወልቃይት ጠገዴ መሪዎችም ሆነ በህዝቡ ላይ ምንም አይነት የመተናኮል እርምጃ እንዳይወስዱ፣ ህወሃት በአካባቢው ያሰማራቸው ታጣቂዎች ከአካባቢው እንዲወጡ፣ ለጠፋው ህይወትና ንብረት የትግራይ ክልል ባለስልጣናት ተጠያቂ በመሆናቸው ለተጎጂዎች ካሳ እንዲከፈል፣ አጥፊ የህወሃት መሪዎችም በህግ እንዲጠየቁና የህዝቡ ህጋዊና ሰላማዊ ጥያቄዎች በአማራ ክልል እልባት እንዲያገኙ ጠይቀዋል።

የሞረሽ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ተክሌ የሻው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሰላማዊ ሰልፉ ኢትዮጵያዊ መልክና ቀለም እንደያዘ ተናግረው፣ የኢትዮጵያ አንድነት መሰረቱ በተለያዩ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ባሳዩት ድጋፍ መጀመሩን ተናግረዋል። በተባበረ ክንድ የህወሃት አመራር እንደሚደመሰስም ለተሰብሳቢው ገልጸዋል። ወያኔ 25 ስልጣን ላይ የቆየው ኢትዮጵያውያን በመከፋፈላቸው ነው ሲሉ የተናገሩት አቶ ተክሌ፣ በጎንደር የተቀጣጠለው ትግል በሌሎች አካባቢዎችም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ ገመቹ ጅፋር በበኩላቸው የህወሃት መሪዎች ለፈጸሙት ግፍና በደል ለፍርድ መቅረብ እንዳለባቸው ተናግረዋል። አንድነት ሃይል ነው ሲሉም ለሰላማዊ ሰልፈኞች የገለጹት አቶ ገመቹ፣ “አንድ ከሆንን እንኳን ለባንዳዎች ለፋሽስቶችም አይበግሩንም” ሲሉ ለሰላማዊ ስልፈኞች ተናግረዋል።

ጊብሰን የተባሉት የጋምቤላ ተወላጅ በበኩላቸው፣ ሁላችን ካልተባበርን ኢትዮጵያ የምትባል አገር አትኖርም ሲሉ ተናግረዋል።

አክቲቪስት ታማን በየነ  ህወሃት በጎንደር ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በመቃወም በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በአንድ ድምጽ ቃል እንዲገባ ጠይቀዋል። “ህወሃቶች ደም ከፍለን ነው የመጣነው የምትሉት የእኛን ደም ለማፍሰስ ከሆነ፣ ደም የሚከፍሉ ገንዘብ የሚከፍሉ ኢትዮጵያውያን አሉን” ሲል ገልጿል። የህወሃት መሪዎችና ደጋፊዎችም ወደ ህሊናቸው ተመልሰው ከኢትዮጵያውያን ጋር በአንድነት እንዲኖሩ መልዕክት አስተላልፏል። ኢትዮጵያ በልጆቿ አንድነቷ ተጠብቆ ለዘላለም ትኖራለች ሲል ለሰላማዊ ሰልፈኞች ተናግሯል።

የህዝብ ጩኸት ከጥይት ይበልጣል ሲሉ በሃገሪቱ በተደጋጋሚ የሚነሱ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ያወሱት ኢትዮጵያውያን ህዝቡ በጋራ በመሆን መብቱን እንዲያስከብር ጥሪን አቅርበዋል።

ነዋሪነታቸው በዚህ በአመሪካ ዋሽንግተርን ዲሲ ከተማና አካባቢዋ የሆነ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች የሚፈጸሙ ግድያዎችን በማውገዝ ተመሳሳይ ሰልፎችን ሲያካሄዱ እንደነበር ይታወሳል።