የጸጥታ ሃይሎች እርምጃ በአስቸኳይ እንዲቆም የአሜሪካ መንግስትና አለም አቀፍ ተቋማት ጠየቁ

ኢሳት (ነሃሴ 3 ፥ 2008)

ወደ 100 ለሚጠጉ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ሃይሎች እርምጃ በአስቸኳይ እንዲቆምና ድርጊቱ አሳስቧቸው እንደሚገኝ የአሜሪካ መንግስትና የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት ገለጡ።

ከቀናት በፊት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በመንግስት የተወሰዱ የሃይል እርምጃዎችን ተከትሎ መግለጫን ያወጣው የአሜሪካ መንግስት በህገ-መንግስት የተቀመጡ የሃገሪቱ ዜጎች መብት እንዲከበር ጥሪን አቅርቧል።

በሃገሪቱ ሰዎች ሃሳባቸውን በሰላም የመግለጽና እንዲሁም የመሰባሰብ መብታቸው መከበር እንዳለበት የአሜሪካ መንግስት ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

መቀመጫውን በዚህ በአሜሪካ ያደረገው ፍሪደም ሃውስ የተሰኘ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋም በበኩሉ የኢትዮጵያ መንግስት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደወስደውን ግድያ በአስቸኳይ እንዲያቆም ማክስኞ ጥሪን አቅርቧል።

የድርጅቱ የአፍሪካ ሃላፊ የሆኑት ቡካሲን ቴትሮቪች የመንግስት ባለስልጣናት ዜጎች ያላቸውን በሰላም የመደራጀትና ሃሳብን የመግለጽ መብት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲያከብሩ አሳስበዋል።

በሃገሪቱ ዲሞክራሲ እንዲኖር ከተፈለገ ህዝቡ እያነሳ ያለው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዙሪያ ስጋቱን ሲገልጽ የቆየው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ አስታውቋል።

በሃገሪቱ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መባባስን ተከትሎ ኢትዮጵያ የከፋ ተብለው ከተፈረጁ ሃገራት መካከል ግንባር ቀደም ልትሆን መብቃቷን ድርጅቱ በቅርቡ ያካሄደው ጥናት ዋቢ በማድረግ ባወጣው ሪፖርት አስፍሯል።

የጅምላ እስራት፣ የዌብሳቶች መዘጋት የኢንተርኔት አገልግሎትን ማቋረጥ እንዲሁም ጦማሪያንና ጋዜጠኞችን ለእስር መዳረግ በኢትዮጵያ እየተባባሰ መምጣቱን ፍሪደም ሃውስ ገልጿል።

በኦሮሚያ ክልል ለወራት የዘለውቀውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን ያወሳው ድርጅቱ ይኸው ተቃውሞ በሳምንቱ መገባደጃ በአማራ ክልል መዛመቱንና በርካታ ሰዎች መሞታቸው አክሎ አመልክቷል።