መስከረም ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ሐሙስ ማምሻውን የተጠናቀቀው የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትርና የፓርቲው ማዕከላዊ
ኮሚቴ አባል የሆኑትን አቶ ጁነዲን ሳዶ በመገምገም ከፓርቲ ኃላፊነታቸው እንዲነሱና ያለመከሰሰ መብታቸው እንዲነሳ
ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በዚሁ መሰረት በቀጣዩ ሳምንት የዓመቱን ሥራውን የሚጀምረው የጨፌ ኦሮሚያ ም/ቤት በሚቀርብለት
ጥያቄ መሰረት ያለመከሰሰ መብታቸውን ያነሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዚህም መሰረት አቶ ጁነዲን ከሳዑዲ ኤምባሲ ጋር ካላቸው ግንኙነት ጋር በተያያዘ በሸብር ወንጀል ተጠርጥረው
ከተያዙት ባለቤታቸው ጋር ወህኒ ይወርዳሉ ሲሉ ምንጫችችን ገልጠዋል።
የአቶ ጁነዲን ባለቤት ወ/ሮ ሐቢባ መሐመድ ከሳዑዲ ኤምባሲ ገንዘብና መጽሐፍት ይዘው ሲወጡ ሐምሌ 9 ቀን 2004
ዓ.ም በፖሊስ መያዛቸውን አገር ቤት የሚታተመው ሰንደቅ ጋዜጣ ይፋ ካደረገ በኃላ ሚኒስትሩ ስለሁኔታው ዘርዘር
ያለምላሸ ሰጥተው ነበር፡፡
በዚሁ መሰረት የአቶ ጁነዲን ወላጅ እናት ባረፉበት ወቅት ጥለው ያለፉትን ኑዛዜ ለማስፈጸም በማሰብ በይዞታቸው ላይ መስጊድ ለማሰራት መንቀሳቀሳቸውን፣ ለዚህም ሲባል በሚኒስትርነታቸው ሳይሆን በግለሰብነታቸው በሌጣ ደብዳቤ የሳዑዲ ኤምባሲ ድጋፍ ጠይቀው በተፈቀደው መሰረት በተከታታይ ገንዘብ እየወሰዱ
መስጊዱ ተሰርቶ ማለቁን አስታውሰዋል፡፡
ሐምሌ 9 ቀን 2004 ዓ.ም መስጊዱ የተመረቀ ሲሆን በዚሁ ምረቃ ላይ የተገኙት የሳዑዲ ኤምባሲ ተወካይ ለመስጊዱ ማጠናከሪያ 500 ቅዱስ ቁርዓን መጽሐፍ እና 50 ሺ ብር ለመስጠት በገቡት ቃል መሰረት ባለቤታቸው በማግስቱ ወደሳዑዲ እምባሲ አምርተው ሰጦታውን ተቀብለው ሲወጡ መያዛቸውን አስታውሰው “ባለቤቴ ቁጥብና ጨዋ ናት” በማለት ፖሊስ አለአግባብ እንዳሰረባቸው ለመግለጽ አማረዋል፡፡
ምንጮች እንደገለጹት ከኦህዴድ ከፍተኛ አመራር መካከል ብዙዎቹ በሙስናና ብልሹ አሰራር እስከአንገታቸው የተዘፈቁ
መሆኑን በማስታወስ ከዚህ አንጻር የአቶ ጁነዲን አድራጎት አዲስ ነገር አለመሆኑን በማስታወስ የሳቸው ጉዳይ ለየት
ብሎ የታየው ከሙስሊሙ እንቅስቃሴ ጀርባ በመሆን መንግስትን ለማስወገድ ከሚሰሩ ኃይሎች ጋር እያበሩ ነው የሚል
ፖለቲካዊ ጥርጣሬ በገዥው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በኩል በመያዙ ነው፡፡
አቶ ጁነዲን ሳዶ በጳጉሜ ወር 2002 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በተካሄደው የኦህዴድ ስድስተኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ
በመተካካት ስም ከኦህዴድ እና ከኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚነት ከተሰናበቱት ወ/ሮ አስቴር ማሞ እና አቶ ሸፈራው
ጃርሶ ጋር ተደባልቀው መነሳታቸው ይታወሳል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኦህዴድን በኢህአዴግ ውስጥ የሚወክሉ የስራአስፈጻሚ አባላት አቶ አለማየሁ አቶምሳ ፣አቶ ሙክታር ከድር፣አቶ ግርማ ብሩ፣አቶ አባዱላ ገመዳ፣አቶ ኩማ ደመቅሳ፣አቶ ሶፊያን አህመድ፣አቶ ድሪባ ኩማ፣አቶ አብዱልአዚዝ አህመድ ሲሆኑ አቶ ዘላላም ጀማነህ ከዚህ ቀደም በሥነምግባር ችግር ተገምግመው ከሥራ አስፈጻሚነት ቦታቸው ተነስተዋል፡፡
የፊታችን ህዳር ወር 2005 በሚካሄደው ድርጅታዊ ጉባዔ በሕመም ምክንያት መልቀቂያ ባቀረቡት የፓርቲው ሊቀመንበሩ አቶ አለማየሁ አቶምሳ ምትክ አዲስ ሊቀመንበር
የሚመረጥ ሲሆን በመተካካት መንፈስ ከኃላፊነታቸው ሊነሱ የሚችሉ ሌሎች አመራሮችም እንደሚኖሩ ምንጫችን ጠቁሟል፡:
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide