(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 30/2010) በደቡብ ጎንደር ስማዳ ወረዳ የጦር መሳሪያ ለማስፈታት በተደረገ እንቅስቃሴ ሁለት ሰዎች ተገደሉ።
በወረዳው ሙጃ ቀበሌ ከአንድ አርሶ አደር ላይ መሳሪያ ለመንጠቅ የተሰማሩ የአገዛዙ ታጣቂዎች ላይ ተኩስ መከፈቱ ታውቋል።
በዚህም አርሶ አደሩና አንድ የሚሊሺያ ታጣቂ መገደላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
አርሶአደሩ መሳሪያዬን አልሰጥም በማለት ከአገዛዙ ታጣቂዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገው አንድ ሚሊሺያ ገድለው መውደቃቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በአማራ ክልል መሳሪያ ለማስፈታት ዘመቻ የተከፈተ ሲሆን ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ ተላልፏል።
በሶስት ምዕራፎች የተከፈለው መሳሪያ የማስፈታት ዘመቻ ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑ ታውቋል።
መሳሪያ የማስፈታቱ ዘመቻ ተጀምሯል።
ካለፈው ሳምንት አንስቶ በአንዳንድ የሰሜን ጎንደር አካባቢዎች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ድንገት ቤት ለቤት ብርበራ የጀመሩት የአገዛዙ ታጣቂዎች ከአርሶአደሮች ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸው እየተነገረ ነው።
ሰሞኑን በደቡብ ጎንደር ስማዳ ወረዳ ከአንድ አርሶ አደር ላይ መሳሪያ ለመንጠቅ የተደረገው እንቅስቃሴ የሰው ህይወት አጥፍቷል።
መሳሪያቸውን እንደማያስረክቡ አቋም በመያዝ ተኩስ የከፈቱት አርሶአደር አንድ ሚሊሺያ መግደላቸውን ነው የኢሳት ምንጮች የገለጹት።
በወረዳው ሙጃ ቀበሌ ነዋሪ ከሆኑት አርሶአደር ላይ መሳሪያ ለመንጠቅ የመጣው የአገዛዙ ታጣቂ ቡድን በደረሰበት ጥቃት ወዲያውኑ የማስፈታት ዘመቻውን ማቆሙንም ለማወቅ ተችሏል።
ባለፈው ሳምንት በጎጃም ዱር ቤቴም መሳሪያቸውን ለመንጠቅ ከተሰማራ የአገዛዙ ሃይል ጋር ውጊያ የገጠሙት አቶ ደርቤ አየለ የተባሉ ስመጥር ጀግና 6 የኮማንድ ፖስት ወታደሮችን በመግደል ራሳቸውንም ማጥፋታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አማካኝነት በአማራ ክልል የከፈተው የጦር መሳሪያ የማስፈታት ዘመቻ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል።
አርሶ አደሩ መሳሪያውን እንደማያስረክብ አቋሙን ለአገዛዙ ባለስልጣናት ማስታወቁን የጠቀሱት የኢሳት ምንጮች በሃይል መሳሪያውን ለመንጠቅ ከሚሞክረው ሃይል ጋርም ሊፋለም መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ኢሳት ያነጋገራቸው አንድ የደቡብ ጎንደር ነዋሪ እንደሚሉት የህወሀት አገዛዝ አማራውን እርስ በእርሱ በሚያጋጭ መልኩ መሳሪያ ነጠቃ ዘመቻውን ጀምሮታል።
በአንድ ወረዳ ያለውን ሁኔታ እንዲህ ይገልጹታል።
ኢሳት በትላንቱ የዜና ክፍለጊዜ እንደዘገበው የመሳሪያ ማስፈታቱ ዘመቻ በሶስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ የሚካሄድ ነው።
በቅደም ተከተል ተፈጻሚ እንደሚሆኑ ቢገለጽም በአንዳንድ አካባቢዎች ሶስቱንም ምዕራፎች በአንድ ጊዜ ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
ፍቃድ ካላቸው ግለሰቦችም የመሳሪያ ነጠቃው በመካሄድ ላይ ነውም ተብሏል።
ጉዳዩ አሳሳቢና የአማራውን ህዝብ ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ህዝቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ የአገዛዙን ዘመቻ እንዲያከሸፍ ዛሬም ጥሪ ተደርጓል።
አርሶአደሮችና በአጠቃላይ ህዝቡ ከወዲሁ እየተነጋገረበት መሆኑን የገለጹት የኢሳት ምንጮች ነጠቃው የማይቆም ከሆነ ርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን ያነጋገርናቸው ይገልጻሉ።