ኢሳት (ጥር 11 ፥ 2008)
በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ዘንድ በየአመቱ በድምቀት የሚከበረው የዘንድሮ የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ረቡዕ ኢትዮጵውያንን ጨምሮ በተለያዩ የአለማችን ሃገራት ተከበረ።
የበአሉ አከባባር ከዋዜማው ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማና በጎንደር ከተማ በርካታ የእምነቱ ተከታዮችና የውጭ ሃገር ጎብኚዎች በተገኙበት በድምቀት መከበሩን ከሃገር ቤት ይተገኘ መረጃ አመልክቷል።
እየሱስ ክርስቶስ በዮሃንስ እጅ የተጠመቀበትን እለት በማሰብ የሚከበረው ይኸው አመታዊ በዓል በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ጃን ሜዳ በደማቅ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓት ተከብሮ መዋሉ ታውቋል።
በካቶሊካዊ ቤተክርስቲያ ተመሳሳይ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶችም የተካሄዱ ሲሆን የሃይማኖት አባቶችም እለቱን በማሰብ ሃይማኖት መልዕክትን አስተላልፈዋል።
ይኸው የጥምቀት በአል ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በሩሲያ በደማቅ ሆኔታ መከበሩን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ከሃገሪቱ ዘግቧል።
የወቅቱ የአየር ጠባይ በሩሲያ እጅግ ቀዝቃዛ ቢሆንም በርካታ የእምነቱ ተከታዮች እለቱን ለማሰብ በበረዷማ ውሃ ውስጥ የጥምቀት ስነስርዓት ማከናወናቸውን የዜና አውታሩ አመልክቷል።
ለሩሲያው የጥምቀት በዓል አከባበር ጎን ለጎን በምስራቅ አውሮፓ የሚገኙ ሃገራትም የዘንድሮውን በዓል በደማቅ ዝግጅት ማክበራቸውን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።