የጥምቀት በአል በከፍተኛ የጸጥታ ቁጥጥርና በቀዘቀዘ ስሜት ተከበረ

ጥር ፲፩ ( አሥራ አንድ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የደረሱን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የዘንድሮውን የጥምቀት በአል ህዝቡ በስርዓቱ ላይ ያለውን ቅሬታ የገለጸበት ነው።
በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፌደራል ፖሊሶችና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጥበቃ ሲያደርጉ ታይተዋል። በሰሜን ጎንደር በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች የጸጥታ ቁጥጥሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠብቆ ታይቷል።
በጎንደር የበአሉ ስነስርዓት ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ ቀዝቅዞ ተከብሯል።
በኮምቦልቻ ስለነበረው የበአል አከባበር የተጠየቀ አንድ ነዋሪ፣ “ ፍሪጅ” ነበር ሲል በአሉ በተቀዛቀዘ ስሜት መከበሩን ገልጿል። በለገጣፎ ለግዳዲ ታቦት አጅቦ ያስገባው ፌደራል ፖሊስ እንደነበር ወኪላችን ተናግሯል።
በባህር ዳር ከተማ ደግሞ የጥምቀት በዓልን ለማክበር ከወጣው ምዕመን ባልተናነሰ ሁኔታ የፌደራልና አድማ በታኝ ወታደሮች እስካፍንጫቸው በመታጠቅ በዓሉን የፍልሚያ ሜዳ አስመስለውት መዋላቸውን የክልሉ ወኪላችን ገልጻለች።
በከፍተኛ ስጋት የተወጠሩት የስርዓቱ ወታደሮች በከተራ በዓል ላይ በየቦታው ህዝቡን ሲያዋክቡና ሲፈትሹ መዋላቸውንም ገልጻለች፡፡
ስናይፐርና የጭስ ቦምብ የታጠቁ የአገዛዙ ወታደሮች በመስቀል አደባባይ አካባቢ በሚገኘው የወጣቶች መዝናኛ ማዕከልና ሙሉ ዓለም አዳራሽ ተከማችተው የታዩ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ለአምልኮ ለመውጣት ያሰበው ምዕመን በመሳቀቅ በቤቱ ሆኖ በመሀላ ለማክበር ተገዷል ብላለች፡፡
በዛሬው የጥምቀት በዓል ታቦታት ወደየ ደብራቸው ሲመለሱ አብዛኛው ምዕመን በመንገድ ጠብቆ ከምዕመኑ ጋር በመቀላቀል አሸኛኘት አድርጓል፡፡ወጣቶች በህብረት እየጨፈሩ ታቦታትን የሸኙ ሲሆን አልፎ አልፎ የአገዛዙን ወታደሮች ሲመለከቱ ‹‹እምቢ በል !! እምቢ በል!! እሽ አትበል !!›› በማለት ተቃውሟቸውን ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፡
በስቴ ከበአሉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የሰማያዊ አባላት ተይዘው የታሰሩ ሲሆን፣ ህዝቡ በበአሉ ላይ ባለመገኘት ተቃውሞውን ገልጿል።
ባህርዳር፣ ደብረታቦር፣ ኮምቦላቻና ሌሎችም ከተሞች ህዝቡ የገዢው ፓርቲ መመሪያን በመጣስ አርማ የሌለውን ሰንደቅ አላማ ይዞ በአሉን አክብሯል።