ሐምሌ ፲፭ ( አሥራ አምስት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አቶ ሃብታሙ አያሌው ከአገር ወጥቶ እንዲታከም በሕክምና ቦርድ የተፈረመበት ማረጋገጫ ቢሰጠውም ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በመዝገብ ቤት በኩል ከአቃቤ ሕግ ጋር የቃል ክርክር ለማድረግ ለማክሰኞ ሀምሌ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል። አቃቤ ሕግ ቅሬታ ባላቀረበበት ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከሕግ አግባብ ውጪ ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ባለቤቱ ወ/ሮ ቤተልሔም አዛናውን ጨምሮ ወዳጅ ዘመዶቹን እንዳሳዘናቸውና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የፍትሕ አካላት ለሕሊናችው ሲሉ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ሚዛናዊ ፍርድ በመስጠት በአግባቡ እንዲሰሩ ስትል ወ/ሮ ቤተልሔም አዛናው የተማጽኖ ጥሪዋን አቅርባለች።
የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አመራር የነበሩት አቶ ዳንኤል ሺበሺ በበኩላቸው አንድ ሕመምተኛ ሕክምና እንዳያገኝ የመከልከሉ ውሳኔ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ ብያኔ ነው ሲሉ አውግዘዋል። በፍርድ ቤት ነፃ የተባለን ሰው አቃቤ ሕግ በዶክተሮች ውሳኔ ላይ የቃል ክርክር እንዲያደርግ መጠየቅና በቀጠሮ ማጉላላት ኢ-ፍትሐዊ ነው ብለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅትን እጩ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የራሳቸውን ዜጋ እየገደሉ የዓለምን ሕዝብ የጤና ችግር አይፈቱም። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊም ማንኛውንም ድጋፍ መስጠት የለበትም። በሃብታሙ አያሌው ላይ የተወሰነው ውሳኔ ፖለቲካዊ ብይን ነው በማለት አቶ ዳንኤል ሺበሺ አበክረው ገልጸዋል።