(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 28/2011)በጠቅላይ ሚኒስትሩና በህክምና ባለሙያዎች ባለፈው ቅዳሜ የተደረገውን ውይይት ተከትሎ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ምላሽ ሰጠ።
በህክምና ባለሙያዎቹ ለተነሱት ጥያቄዎች መፍትሄ የሆኑ ውሳኔዎችን ማሳለፉንም አስታወቋሎ።
የህክምና ባለሙያዎቹ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የነበረውን ውይይት በተመለከተ ቅሬታ ማቅረባቸው ታውቋል።
በውይይቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገቢው መንገድ አላስተናገዱንም ብለዋል አንዳንድ የህክምና ባለሙያዎች።
ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጥያቄዎቹን እየመለስኩ ነው የተቀሩትንም ግብረሃይል ተቋቁሞ በመስራት ላይ ነው ሲል ዛሬ አስታውቋል።
ለሳምንታት ሲካሄድ የነበረው የህክምና ባለሙያዎችን ተቃውሞ ተከትሎ ያለፈው ቅዳሜ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ውይይት ጠርተው ነበር።
ከሶስት ሺህ በላይ የህክምና ባለሙያዎች በተገኙበት በዚሁ ውይይት የጤና ፖሊሲው ላይ ያነጣጠሩ፣ የህክምና ባለሙያዎችን ክብር ይነፍጋሉ፤ ጥቅም ያሳጣሉ በሚል በርካታ ጥያቄዎች መነሳታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ጋር ሆነው የህክምና ባለሙያዎቹን ያነጋገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሃገሪቱ የማሻሻያ ርምጃዎች እየተወሰዱና ማሻሻያው ካልደረሰባቸው ተቋማት አንዱ የጤናው ዘርፍ በመሆኑ በቀጣይ ትኩረት ይደረግበታል የሚል አቋም አንጸባርቀዋል።
ከውይይቱ በኋላ በተለያዩ መድረኮች ሀሳባቸውን የሰጡ የውይይቱ ተሳታፊ የህክምና ባለሙያዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅዳሜ ውይይት ለባለሙያዎቹ ጥሩ ስሜት የሰጠ አይደለም በሚል ቅሬታ አቅርበዋል።
በውይይቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሷቸው ሀሳቦችና የተጠቀሟቸው አገላለጾች ተገቢ አይደሉም በሚል ቅሬታ ያቀረቡት አንዳንድ የህክምና ባለሙያዎች የመብት ትግላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በዛሬው እለት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይፋ የተደረገውና 13 ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የተላለፈባቸው የመፍትሄ ሀሳቦች በመንግስት በኩል ምላሽ ለመስጠት ፍላጎት መኖሩን ያሳየ ነው ተብሏል።
ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በዝርዝር ባወጣው ውሳኔዎች ላይ እንደተመለከተው ከመጪው ወር ጀምሮ 4ሺህ ለሚጠጉና ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙ ከፍተኛ ሃኪሞች ደሞዝ፤ መደብና ጥቅማጥቅም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚሸፈን ይሆናል።
ለከፍተኛ ህክምና በግል ትምህርታቸውን መከታተል ለሚፈልጉትም ፍቃድ መሰጠቱን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ከሚቀጥለው ወር ጀምሮም ሃኪሞች የትምህርት ማስረጃቸውን ለማግኘት የሚከፍሉት ግማሽ ሚሊየን የሚጠጋ ብር እንደሚቀርና እንደማንኛውም የመንግስት ዩኒቨርስቲ ተመራቂዎች ወጪ በመጋራት ህግ የሚስተናገዱ ይሆናሉ ነው የተባለው።
ጥቅማጥቅምን የደምወዝ ጭማሪንና ምደባን በተመለከተ በክልልና በፌደራል ደረጃ መሻሻል እንዲደረግበት ከውሳኔ ላይ ተደርሷል።
የጤና ፖሊሲውም በመከለስ ላይ መሆኑን የገለጸው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የህክምና ባለሙያዎች በሚኒስቴሩ ድረ ገጽ ውስጥ በመግባት የማሻሻያ ሀሳብ እንዲሰጡበት ጥሪ አድርጓል።
በዛሬው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መግለጫ ላይ ተለማማጅ ሀኪሞችን፤ ከግል የትምህርት ተቋማት የሚመረቁ የህክምና ባለሙያዎችን፤ የተመለከቱ የማሻሻያ ውሳኔዎች መደረጋቸው ተመልክቷል።
በህክምና ባለሙያዎች የተነሱ ሌሎች ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል ግብረሃይል ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።