የጣቁሳ ወረዳ መምህራን የስራ ማቆም አድማ አደረጉ
( ኢሳት ዜና መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ/ም ) በማእከላዊ ጎንደር ዞን በጣቁሳ ቀረዳ የሚገኙ ከ70 በላይ በሚሆኑ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ የወረዳው መምህራን የስራ ማቆም አድማ ያደረጉት ከቤት መስሪያ ቦታ ጋር በተያያዘ ከማዘጋጃ ቤቱ ጋር በተፈጠረ ችግር ነው።
መንግስት ባወረደው መመሪያ መሰረት በ24 ማህበራት የተደራጁ መምህራን ቦታ ይሰጠናል ብለው ሲጠባበቁ ምንም መልስ ባለማግኘታቸው ጉዳዩን ወደ ክልል ማመልከታቸውንና ክልሉ ሁሉም ወረዳዎች የተደራጁ የመምህራንን ማህበራት ቁጥር በመላክ በክልል በጀት ሲያሲዙ የጣቁሳ ወረዳ መምህራን መረጃ ባለመላካቸው ባጀት ሳይያዝላቸው በመቅረቱ አድማውን ለማድረግ ተገደዋል። መምህራን በደልጊ ከተማ ተሰባስበው ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል ። መምህራንም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ መልስ የማይሰጣቸው ከሆነ የሥራ ማቆም አድማውን እንደሚቀጥሉበት አስጠንቅቀዋል።