መስከረም ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የጎንደር ዩኒቨርስቲ መምህራንንና ሰራተኞች ዛሬ በሳይንስ አምባ አዳራሽ ላይ ስብሰባ የተካሄደ ቢሆንም፣ መምህራኑ በጩኸት እና በፉጨት ተቃውሞ በማሰማታቸው እንዲበተን ተደርጓል።
ስብሰባውን የመሩት የቀድሞው የትምህርት ሚ/ር ዶ/ር ስንታየሁ ወልደሚካኤል ሲሆኑ ፣ ንግግር ሲጀምሩ የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ በጩኸት አቋርጧቸዋል። ስብሰባው መቀጠል እንደማይቻል የተረዱት ሰብሳቢዎቹ በእረፍት አሳበው ከ20 ደቂቃዎች በሁዋላ ስብሰባውን በትነውታል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ደሳለኝ መንገሻ የስብሰባው ርዕስ እና አጀንዳ ከፓለቲካ ወደ እቅድ አፈፃፀም ዛሬ ከሰአት ይቀጥላል ቢልም መምህራን ግን ተቃውሟቸውን እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡ ሰው እየተገደለና እየታፈነ እኛ ሰላም ያለ ለማስመሰል አንሰበሰብም በማለት ተቃውሟቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የባህርዳር ዩኒቨርስቲ መምህራንም ለ2 ሳምንት ሊሰጣቸው የነበረውን የፖለቲካ ስልጠና በመቃወማቸው ስብሰባው እንዲበተን ተደርጓል።
በአማራ ክልል በሚካሄደው የህዝባዊ እምቢተኝነት ትግል የተቃውሞው ማእከል የሆኑት ጎንደርና ባህርዳር ዩኒቨርስቲዎች መምህራን እያሳዩት ያለው የአቋም አንድነት፣ ገዢው ፓርቲ ዩኒቨርስቲዎቹ ስራ ሲጀምሩ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ሊጀምሩ ይችላሉ የሚለውን ስጋት አባብሶታል።
የመምህራን ተቃውሞ አድማሱን እያሰፋ ሲሆን፣ በሰ/ሸዋ ዞን መርሐቤቴ ወረዳ አለም ከተማ ፣ አለም ከተማ መሠናዶ:፣ አርበኞች አጠ/2ኛ ደረጃ እና አለም ከተማ 1ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ከመስከረም 18፣ 2009 ዓም ጀምሮ ለተከታታይ 6 ቀናት ሊሰጥ የነበረው ስልጠና መምህራኑ በዝምታ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ተከትሎ እንዲቋረጥ ተደርጓል።
የዓለም ከተማ መሰናዶ መምህራን ሰብሳቢዎቹን የወረዳውን አስተዳዳሪ አቶ ዘውዴ እና የብአዴን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰጠኝን “ስርዓቱ ሊለወጥ ስለማይችል ሰልችቶናል፣ ሀሳብ የለንም” ብለው የነገሩዋቸው ሲሆን፣ ሀሳብ የሚሰጥ መጥፋቱን የተመለከቱት አስተዳዳሪው “ስልጠናው ሳይሰጥ ትም/ት አትጀምሩም፣ በኛ በኩል ከአቅማቸን በላይ ነው፣ የክልሉ ወይም ከዚያ በላይ ያለው አካል ይፈታዋል “በማለት ማስፈራሪያ ቃሎችን ተናግረው ተመልሰዋል።
በላሊበላ ከተማ በሚደረገው የመምህራን ስብሰባም መምህራን 4ቱን ቀናት ምንም ነገር ሳይናገሩ ያሳለፉ ሲሆን፣ ሰብሳቢዎቹ “ እያንዳንዳችሁን በሚስጢር እናጠናችሁዋለን” በማለት መምህራኑን ለማስፈራራት ሞክረዋል። እነሱ የመለመሉዋቸው መምህራን እንዲናገሩ ለማግባባት ቢሞክሩም እንዳልተሳካለቸው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ መምህራን ገልጸዋል።
በአቸፈር ወረዳ በዱርቤቴ ከተማም እንዲሁ መምህራን በዝምታ ተቃውሞአቸውን መግለጻቸውን ከስፍራው የደረሰን ዜና ያመለክታል። መምህራኑ ባለፉት 25 ዓመታት ያየነው ለውጥ የለም በማለት በስብሰባው ላይ አስተያየት ላለመስጠት መወሰናቸውን መምህራን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል አሁንም በጎንደር የንግድ ድርጅቶችን የማሸግ እንቅስቃሴው ቀጥሎአል። የተወሰኑ የንግድ ድርጅቶችን በመዝጋትና ቅጣት በመጣል፣ የተወሰኑትን ደግሞ በመዝለል ነጋዴውን ማህበረሰብ ለመከፋፈል የሚጠቀሙበት ስልት ነው በማለት የትግሉ አስተባባሪዎች ይናገራሉ። አገዛዙ ሁሉም የንግድ ድርጅቶች በአስቸኳይ እንዲከፈቱ የማያደርግ ከሆነ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰድ ይጀምራሉ ብለዋል።