(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 21/2010)
ትላንት የአርበኛ ጎቤ መልኬን አንደኛ ሙት ዓመት መታሰቢያና የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴ አባላትን ከእስር መለቀቅ ምክንያት በማድረግ በቆላማው የጎንደር አካባቢ ህዝቡ ደስታውን ሲገልጽ መዋሉ ታወቀ።
በተኮስ እሩምታና በመኪናጥሩምባ የታጀበው የደስታ መግለጫ ትዕይንት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የጣሰ የህዝብ እርምጃ እንደሆነ ም ታውቋል።
አርበኛ ጎቤ መልኬ ከጎንደሩ ህዝባዊ እምቢተኝነት በኋላ ስማቸው ጎልቶ የወጣ ይሁን እንጂ በፊትም በልጅ አዋቂው ዘንድ የተመሰከረላቸው ጀግና ነበሩ። ለወገናቸው ጠበቃ፡ መጠቃትን የማይፈልጉ፡ ለሀገራቸው የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ምንጊዜም ዝግጁ ሆነው የሚጠብቁ በአርዓያነት የሚጠቀሱ አርበኛ ናቸው። በተለይ በጎንደር ከተቀሰቀሰው ህዝባዊ ዕምቢተኝነት ጋር በተያያዘ የህዝቡን ትግል ለመምራት ፊት ለፊት በአርበኝነት ብቅ ማለታቸው በተቀረው የኢትዮጵያ ክፍልም ስማቸውን እንዲነሳ አደረገው። በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ የህዝብን ጥያቄ በሃይል ለመጨፍለቅ በመወሰን እርምጃ መውሰዱን ተከትሎ አርበኛ ጎቤ ጥቂቶችን ይዘው ጫካ ሸፈቱ።
ንብረታቸውን፡ ሀብታቸውን በሙሉ ትተው ወደ ትግል የገቡት አርበኛ ጎቤ ከአንድ ዓመት በላይ በሰሜን ጎንደር በዱርና በጫካ ሆነው የአገዛዙን ወታደሮች ውጊያ በመግጠም አያሌ ገድሎችን የፈጸሙ እንደሆነ ይነገርላቸዋል።
በዚህም በርካታ የአገዛዙን ታጣቂዎች በመግደልና በማቁሰል የህዝብ ትግል እንዳይቆም ያደረጉ ናቸው። አገዛዙ የአርበኛውን ጥቃት ለመመከት መደበኛ ጦሩን እስከማሰማራት ደርሷል።
ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ አርበኛ ጎቤን ለመያዝ የተደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። በመጨረሻም አገዛዙ በገንዘብ በደለላቸው የቤተሰብ አባል ተገደሉ። የካቲት 21 2009 ዓም።
ትላንት የአርበኛ ጎቤ አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ይውላል። እንደልማድም በተኩስ፡ እሩምታ መታሰቢያ መደመቅ ይጠበቅበት ነበረ። ሆኖም ማንኛውንም ህዝባዊ ትዕይንቶችን የሚከለክለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የአርበኛ ጎቤን አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ሊያቀዘቅዘው ይችላል የሚል ስጋት በብዙዎች ዘንድ አደረ። ትላንት የካቲት 21 2010 ዓም የሆነው ግን የተለየ ነበር። አስቸኳይ አዋጁን በጣሰ ልዩ ትዕይንት የአርበኛው መታሰቢያ በቆላማው ጎንደር ዙሪያ ባሉ አከባቢዎች በድምቀት ተካሂዷል። በመሳሪያ ተኩስና በመኪና ጥሩምባ በደመቀው በዚሁ ትዕይንት አርበኛ ጎቤ መልኬ ተዘክሯል።
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የጣሰው የትላንቱ ትዕይንት ከእስር ለተፈቱት የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴ አባላትም ደስታን ለመግለጽ እንደሆነም ተመልክቷል። ከግማሽ ሰዓት በላይ የቆየ የቀለጠ የተኩስ እሩምታ በተካሄደበት ወቅት በአከባቢው የኮማንድ ፖስት የነበረ ቢሆንም የህዝቡን እርምጃ ማስቆም እንዳልተቻለ ታውቋል። ከየአቅጣጫው ውግዘትና ተቃውሞ እየቀረበበት ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ህዝብ እየጣሰው መሆኑ የቀጠለ ሲሆን ሰሞኑን ነቀምት ደምቢዶሎ ላሊበላ ጎንደር አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣስ ህዝባዊ ንቅናቄ ማድረጋቸው የሚታወቅ ነው።