ኢሳት (ሃምሌ 28 ፥ 2008)
በሳምንቱ መጨረሻ በኦሮሚያ ክልል እንዲሁም በአማራ አንዳንድ አካባቢዎች ለታቀደው ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ የጎንደሩን ህዝባዊ ትዕይንት ያስተባበሩ አካላት ድጋፍ ሰጡ። መላው የጎንደር አማራ ኢትዮጵያውያን በሚል ስያሜ የተሰባሰበውና ዕሁድ ሃምሌ 24 ፥ 2008 በጎንደር ከተማ የተካሄደውን ደማቅ ህዝባዊ ትዕይንት ያስተባበሩት ወገኖች ልምዳቸውን ከማካፈል ባሻገር አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም በሁሉም መንገድ ከጎናቸው እንደሚቆሙ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
“በእነዚህ ለሰው ልጅ ክብር ቤሌላቸው ይሉኝታ የሚባል ባልፈጠረባቸው ከ25 አመታት በላይ እንድንታሰር እንድንገረፍና እየተገደልን ብዙ ወገኖቻችንን እንድናጣ ተደርገናል” በሚለውና የተቃውሞን መነሻ የሚዘረዝረው መግለጫ ሲቀጥል፣ “አሁን ደግሞ ቤት ድረስ ዘልቀው በመግባት የቤተሰብ ዘር ማጥፋት በስፋት ጀምረውታል ፥ ይህ ግፍ አጅግ በመብዛቱ ልንሸከመው ስላልቻልን እኛ የጎንደር አማራ ኢትዮጵያውያን “ጅብ ከሚበላህ ጅብ በልተህ ተቀደስ” በሚሉት የአባቶቻችንን አባባል ለመተግበር በሰላም ሲመጡብን በሰላም፣ በሃይል ሲመጡብን በሃይል እያስተናገድን እንገኛለን ፥” በማለት ሌሎችም ይህንን አርአያነት እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በሃይል ሲመጡብን በሃይል ማቆም የምንችለው መሳሪያ ስላለን ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች አማራጮችም ተዘጋጅተን ነበር ሲሉ ልምዳቸውን ዘርዝረዋል።
ለሰላማዊ ጥያቄው በጎንደር የሚገኙ የፌዴራልና የክልል ፖሊሶች መሳሪያቸውን ባለማንሳታቸውና የህዝቡን ጥሪ ባለመቀበላቸው የሚያመሰግነው መግለጫ፣ በኦሮሚያና በሌሎች የአማራ ክልል የሚገኙ ከተሞችም ይህንን አርአያነት በመከተል ሰልፎቹ በሰላም እንዲጠናቀቁ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሃይል ምላሽ የሚከተል ከሆነ፣ በጎንደር ህዝባዊ ትዕይንት ወቅት የነበሩ ዝግጅቶችም ለተሞክሮ አሰራጭተዋል፥ በታጣቂዎች የሃይል የሚሰጥ ከሆነ፣ መሳሪያ ያልያዙ ወንዶች በድንጋይ ምላሽ ለመስጠት እንዲሁም ሴቶች በኮዳና ላስቲክ ውሃ፣ እንዲሁም ብትን ሚጥሚጣ በመያዝ ለሃይል አጸፋው ምላሽ በመስጠት መሳሪያ በመንጠቅ፣ የበላይነትን ለመያዝ ዝግጅት እንደነበር ዘርዝረዋል።
በኦሮሚያ ክልል እና በአማራ ክልል እንዳንድ አካባቢዎች ለታቀደው ሰልፍ በዚህ መልክ ልምድን ያካፈለውና በሰላም እንዲጠናቀቅ የጸጥታ ሃይሎች ጣልቃ እንዳይገቡም ያሳሰበው መግለጫ ሲያጠቃልልም፣ “በቅርበት ባላችሁበት በሰልፉ እንገኛለን፣ ከዚያ ባሻገር ወደሃይል እርምጃ ካስገቧችሁ ግን እኛም ከጎናችሁ እንደርሳለን በርቱ” ሲል አጋርነቱን ገልጿል።