ኢሳት ዜና (ግንቦት 11 ፥ 2008)
በቅርቡ በተለያዩ ክልሎች የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ከ230 ሺ በላይ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቀሉ።
ሃገሪቱ ለምግብ እርዳታ ለተጋለጡ ዜጎች በቂ ምላሽን ባላገኘችበት በአሁኑ ወቅት የጎርፍ አደጋ እያደረሰ ያለው ጉዳት ተጨማሪ ስጋት ፈጥሮ መገኘቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሃሙስ አስታውቋል።
በምስራቃዊ ኢትዮጵያ እና በሶማሊ ክልል ካለፈው ወር ጀምሮ የደረሰው ይኸው የጎርፍ አደጋ በአጠቃላይ 237 ሺ ሰዎችን ከመኖሪያ ቀያቸው እንዳፈናቀለም ድርጅቱ በዚሁ ችግር ዙሪያ ባውጣው ሪፖርት አመልክቷል።
የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው በተለያዩ ክልሎች በደረሰ የጎርፍ አደጋ በትንሹ የ150 ሰዎች ህይወት ማለፉን በመግለጽ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎች ሊፈናቀሉ እንደሚችሉም ገልጸዋል።
የብሄራዊ አደጋ መከላከያ ኮሚሽን በተለያዩ አካባቢዎች በደረሰው የከባድ ዝናብና የጎርፍ አደጋ 36ሺ ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ሰብል ሙሉ ለሙሉ መውደሙን ገልጿል።
ከ30ሺ ለሚበልጡ የቤት እንስሳት ሞት ምክንያት የሆነ ይኸው የጎርፍ አደጋ እስከ ቀጣዩ ነሃሴ ወር ድረስ የሚቀጥል በመሆኑም ከቀያቸው የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩላቸው በተያዘው 2016 የፈረንጆች አ ም እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በጎርፍ አደጋ ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ በቅርቡ ትንበያ መስጠቱ ይታወሳል።
የጎርፍ አደጋው በመሰረተ-ልማቶች ላይ ያደረሰው ጉዳትም ለምግብ ተረጂዎች በወቅቱ ድጋፍ እንዳይደርስ ተፅዕኖ ማሳደሩንም የእርዳታ ድርጅቶች በመግለጽ ላይ ናቸው።
የአደጋ መከላከያ ኮሚሽን በተጨማሪ የጎርፍ አደጋ ይደርስባቸዋል ከተባሉ አካባቢዎች ሰዎችን ወደከፍታ ስፍራዎች የማዘዋወር ስራ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ከተጋለጡ ከ 10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሚያስፈልገው የገንዘብ ድጋፍ በበቂ ሁኔታ ባለመገኘቱ ሳቢያ የድርቁ ጉዳት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የእርዳታ ተቋማት በድጋሚ አሳስቧል።
በተለይ ስድስት ሚሊዮን ህጻናት ህይወት በአደጋ ላይ መሆኑን የገለጹት ድርጅቶቹ የህጻናቱን ህይወት ለመታደግ እስከ ሃምሌ ወር ድረስ 700 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ መገኘት እንዳለበትም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከውጭ ንግድ ወደ አምስት ቢሊዮን ዶላር ገቢን ለማስገኘት እቅድ ቢይዝም የእቅዱ ግማሽ ብቻ መገኘቱን ለመረዳት ተችሏል።