ግንቦት ፲፩ (አስራ አንድ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከተቋቋመ 17 ወራትን ያስቆጠረው የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል ለ4ኛ ዙር በወታደራዊ፣ ፖለቲካ፣ መረጃ እና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ያሰለጠናቸውን ታጋዮች አስምርቋል።
ስልጠናው ታጋዮቹ ለሚጠብቃቸው ጥብቅ ግዳጅ በአካል እና በመንፈስ ዝግጁ የሚያደርጋቸው መሆኑን ህዝባዊ ሃይሉ ገልጿል።
ከ4ኛው ዙር ስልጣኞች መካከል አንዱ የሆነው አሊ ሞሃመድ ስልጠናው ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት የሚያስችል መሆኑን ገልጾ፣ ትግሉ ሪጅም ጊዜ ይወስዳል ብሎ እንደማያምን አክሏል።
አዲሲቷ ኢትዮጵያን ለመገንባት በምናደርገው ትግል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ምን ያገባኛል የሚለውን ትቶ ትግሉን እንዲቀላቀል ጥሪ አቅርቧል።
አብዲሳ አጋ የተባለው ተመራቂም እንዲሁ በስልጠናው ምንም አይነት ችግር እንዳላጋጠመው ገልጾ፣ መሰረታዊ የሆኑትን ስልጠናዎችን በመውሰዱ ወታደራዊ ብቃት ማዳበሩን ገልጿል።
“አንድ ህዝብ ነን አንድ አገር እንገንባ” የሚለው አብዲሳ አጋ መልእክቱን በኦሮምኛና በአማርኛ አስተላልፏል።
ከ2 ሺ ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዞ የግንቦት 7ትን ህዝባዊ ሃይል መቀላቀሉን የገለጸው አለም አደመ በበኩሉ፣ ህዝባዊ ሃይሉን ስቀላቀል ነጻነቴን ያገኘሁ ያክል ነው የተሰማኝ ብሎአል።
“የደፈረና የቆረጠ ሰው ይህን ቦታ ያገኛል” ያለው አለም ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትግሉን እንዲቀላቀል በአማርኛና በጋሞኛ መልእክቱን አስተላልፋል።
የግንቦት7 ህዝባዊ ሃይል ድርጀቱን ለመቀላቀል የሚፈልጉ ሁሉ መረጃዎችን በድረገጽ፣ በፌስቡክና በስልክ ማግኘት እንደሚችሉ ገልጿል።