ኢሳት (ጥቅምት 23 ፥ 2009)
የግብፅ ተቋማት ለኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሃይሎች እርዳታ እንደሚለግሱ በቂ መረጃ አለን ሲሉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ገለጹ። አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ መንግስታቸው ከግብጽ መንግስት ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚሰሩ ጸረ-ልማት የግብፅ ተቋማትን እየለየን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የፓርላማ አባላት ላነሱት ጥያቄ መልስ የሰጡት አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ፣ ኢትዮጵያ ለግብፅ መንግስት ቀጥተኛና ግልጽ ጥያቄ ማቅረቧን ገልጸው፣ የግብፅ መንግስት እነዚህ ሃይሎች በእኛ ስር አይደሉም ብሎ ነግሮናል ሲሉ ለፓርላማውን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከግብጽ ጋር የዲፕሎማቲሲ ግንኙነቷን እንደምትቀጥል በዚሁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር የገለጹት አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ፣ የግብጽ መንግስት ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚሰሩ ጸረሰላም ተቋማትን እንዲቆጣጠርላቸው ጠይቀዋል።
በውጭ ባሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ላይ በትውልደ ኢትዮጵያውያን ጥቃት መፈጸማቸውንና እነዚሁን ተቃዋሚዎች መንግስታት ካላስቆሙልን እኛም የእነሱን ኤምባሲዎች አንጠብቅም ሲሉ አቶ ሃይለማሪያም ለፓርላማው ተናግረዋል።
በሌላ ዜና ግብፅና ኤርትራ በኢትዮጵያ ውስጥ ተቃውሞ እንዲነሳ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ አቶ ካሳ ተክለብርሃን ለሱዳን ትሪቢዩን ገለጹ።
የኢትዮጵያ የፌዴራል ጉዳዮች እና የአርብቶ አደር ልማት ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለብርሃን፣ ግብፅና ኤርትራ ኢትዮጵያን ለማተራመስ እጃቸውን እንዳለበት በቂ መረጃ አለን ሲሉ ለሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ ገልጸዋል።
የግብጽ መንግስት ለኦሮሞ ነጻነት ግንባር ድጋፍ ይሰጣል ያሉት አቶ ካሳ ተክለብርሃን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ የተወሰደው የካቢኔ ሽግሽግ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል የተወሰደ እርምጃ እንጂ በህዝባዊ ተቃውሞ ግፊት የተደረገ ሽግሽግ አለመሆኑን ለዚሁ ጋዜጣ አስረድተዋል።
የግብጽ መንግስት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ ተቃውሞ ጣልቃ አለመግባቱን በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ በሰጠው ምላሽ ማስተባበሉ ይታወሳል። የግብፅ ፕሬዚደንት አብደል ፈታህ አል ሲሲ ሃገራቸው፣ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳልገባችና መግባት እንደማትፈልግ በመግለጽ የኢትዮጵያን ክስ በተደጋጋሚ አስተባብለዋል።
በአባይ ግድብ ጉዳይ ባለመግባባት ውስጥ የቆዩት ሁለቱ ሃገራት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ እንዲህ ያለ ውዝግብ ውስጥ ሲገቡ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑም ታውቋል።