የግብፅ መንግስት 45 የኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሱዳንና ማሊ ዜጎችን ወደሃገራቸው መለሰ

ኢሳት (ጥር 10  ፥ 2008)

የግብፅ መንግስት በህገ-ወጥ መንገድ ወደሃገሪቱ ገብተዋል ያላቸውን 45 የኢትዮጵያ፣ ኬንያ ሱዳንና ማሊ ዜጎችን ወደሃገራቸው መመለሱን ማክሰኞ ገለጠ።

በሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ገብተዋል የተባሉት እነዚሁ ስደተኞች ወደ እስራኤልና ሊቢያ የመጓዝ እቅድ እንደነበራቸው ዘ-ካይሮ ፖስት ጋዜጣ አስነብቧል።

ስደተኞቹ ወደሃገራቸው የመመለሱ ሂደትም በግብፅ ከሚገኙ ኢምባሲዎች ጋር ምክክር ተካሂዶበት መሆኑን ጋዜጣው የደህንነት ምንጮች ዋቢ በማድረግ በዘገባው አመልክቷል።

ይሁንና ከስደተኞቹ መካከል ምን ያህሉ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ የተገለጸ ነገር የሌለ ሲሆን፣ ግብፅ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ያለፍላጎት ወደሃገራቸው ስትመልስ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑም ታውቋል።

በህዳር ወር ብቻ ወደ 22ሺ የሚጠጉ የተለያዩ ሃገራት ስደተኞች ወደግብፅ በህገወጥ መንገድ መግባታቸውንም የግብፅ መከላከያ ሰራዊት ቃል አቀባይ መሃመድ ሰሚር ለጋዜጣው አስረድተዋል።

የግብፅ የጸጥታ ሃይሎች የሃገሪቱን ድንበር በማቋረጥ ወደእስራዔል ለመግባት በሚሞክሩ ስደተኞች ላይ የተኩስ እርምጃን እንደሚፈጽሙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ይገልጻሉ።

ከአንድ ወር በፊት 15 የአፍሪካ ስደተኞች አስከሬን በድንበሩ አካባቢ መገኘቱን ዘ-ካይሮ ፖስት ጋዜጣ በዘገባው አስነብቧል።

በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት በመሸሽ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ወጣት ወደጎረቤት ሱዳንና የተለያዩ ሃገራት በመሰደድ ላይ እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።