ኢሳት (ጥር 29 ፥ 2009)
የደቡብ ሱዳን አማጺያን በሳምንቱ መገባደጃ በግብፅ አየር ሃይል የአየር ጥቃት ተፈጽሞብናል ያሉትን ቅሬታ የግብፅ መንግስት አስተባበለ።
ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር በአለመግባባት ውስጥ የሚገኙት አማጺያን የግብፅ አየር ሃይል ከቀናት በፊት በዩኒቲ ግዛት በሚገኙ ሶስት ስፍራዎች የአየር ጥቃት ተፈጽሞብናል ሲሉ ቅሬታ ማቅረባቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ባለፈው ወር በግብፅ ጉብኝት ያደረጉት የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልባኪር ከግብፅ መንግስት ጋር የተለያዩ ስምምነቶችን ደርሰው እንደነበር በስፋት መዘገቡ ይታወሳል።
ሁለቱ መሪዎች ያደረጉት ምክክር ከደቡብ ሱዳን አማጺያን በተጨማሪ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ስጋትን አሳድሮ እንደነበርም የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ይሁንና የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት፣ ጉብኝት የኢትዮጵያ ጥቅምን የሚጎዳ አይደለም ሲሉ ይፋዊ ማስተባቢያን ሰጥተዋል።
የደቡቡ ሱዳን አማጺያን ሁለቱ መሪዎች ለሁለት ቀን ባካሄዱት ምክክር የደቡብ ሱዳን አማጺያንን በጋራ ለማጥቃት ስምምነት አድርገው እንደነበርም በቅርቡ አስታውቀዋል።
ይህንኑ ቅሬታ ተከትሎ የአማጺ ቡድኑ ከቀናት በፊት የግብፅ አየር ሃይል የአየር ጥቃት ተፈጽሞብናል ሲሉ ቅሬታን ያቀረቡ ሲሆን፣ የግብፅ መንግስት በበኩሉ በአማጺያኑ ላይ የፈጸመው ጥቃት እንደሌለ ማስተባበያ መሰጠቱን አልመስሪ የተሰኘ ጋዜጣ ሰኞ ዘግቧል።
የሃገሪቱ ውጭ ጉዳን ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑ አህመድ አቡ ዘይድ ሃገራቸው በሌላ ሃገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደማትገባና አማጺያን ቡድን ያቀረቡት ስሞታም መሰረት የሌለው ነው ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
የደቡብ ሱዳን መንግስትና አማጺያን ቡድኑ ባለፈው አመት የጋራ ብሄራዊ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ስምምነት ቢደርሱም ብዙም ሳይቆይ ግጭት መቀስቀሱ ይታወሳል።
መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ አድርገው የነበሩት የአማጺያን ቡድን ሃላፊ ሪክ ማቻር በተደረሰው ስምምነት መሰረት የምክትል ፕሬዚደንትነት ስልጣን ቢሰጣቸውም የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ ማቻር ከሃገሪቱ መኮብለላቸው ይታወቃል።
የደቡብ ሱዳን እና የኢትዮጵያ መንግስት ከወራት በፊት አንደኛው የሌላኛውን ሃገር አማጺ ላለመደገፍ ያደረጉትን መግባባት ተከትሎ ኢትዮጵያ ሪክ ማቻር ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው እንዳይገቡ እገዳን ጥላ ትገኛለች።