ኢሳት (ግንቦት 22 ፥ 2008)
ሰሞኑን የመንግስት ቃል አቀባይ ሃገሪቱ ከግብፅ ጋር ግድቡን እንዲያጠና የተቋቋመው ቡድን ጥናቱን እስኪያጠናቅቅ ድረስ ግንባታ ለማቋረጥ የተገባ ቃል የለም ሲሉ የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ የግብፅ መንግስት ከኢትዮጵያ ማብራሪያን ጠየቀ።
ቃለ አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የግንቦት 20 በዓል አከባበርን አስመልክቶ ኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን ባለፈው አመት የሶስትዮሽ ስምምነት ቢያደርጉም፣ ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ለማቋረጥ የገባችው ቃል የለም ሲሉ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ይሁንና፣ የመንግስት ቃል አቀባዩ የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ ግብፅ አዲስ አበባ በሚገኘው ኢምባሲዋ በኩል ማብራሪያ መጠየቋን አህራም የተሰኘ የሃገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል።
ከካይሮ በሶስቱ ሃገራት መሪዎች መካከል የተደረሰን ስምምነት ተከትሎ ግብፅ ግድቡን እንዲያጠና የተቋቋመው ቡድን ስራውን ጀምሮ እስከሚያጠናቅቅ ድረስ ግንባታ እንደሚቋረጥ በመንግስት ደረጃ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።
ይሁንና፣ ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ እንዲያጠኑ የተመረጡ ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች እስከ አሁን ድረስ ስራቸውን እንዳልጀመሩ ታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሰጠው ማብራሪያ ዙሪያ ዝርዝር መግለጫን ከመስጠት የተቆጠቡት የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ግብፅን የሚጎዳ ድርጊት እንደማይከተሉ ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸዋል።
በመሪዎች ደረጃ በሶስቱ ሃገራት የተደረሰው ስምምነት በግብፅ በኩል በተደጋጋሚ ማብራሪያ ቢሰጥበትም፣ የኢትዮጵያና የሱዳን ባለስልጣናት ዝርዝር ጉዳይን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
አስር የመግባቢያ ነጥቦች አካቷል የሚባለውን ይህንኑ ስምምነት ምክንያት በማድረግ ግብፅ ከኢትዮጵያ በሚሰጡ መግለጫዎች ዙሪያ ማብራሪያን ብትጠይቅም ግብፅ በምትሰጠው መረጃ ዙሪያ ግን ከኢትዮጵያ ወገን የሚሰጥ ምላሽ አለመኖሩንም ለመረዳት ተችሏል።
ስራውን በቅርቡ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የቴክኒክ የባለሙያዎች ቡድን ስራውን በሚጀምር ግዜ በግድቡ ግንባታ ላይ ተግባራዊ የሚደረጉ ጉዳዮች ይኑር አይኑር የተገለጸ ነገ የለም።