የግብፅ ልዑካን ቡድን በአባይ ግድብ ዙሪያ ከሱዳን ጋር ለመምከር ካርቱም ገባ

ኢሳት ዜና (ጥቅምት 2 ፣ 2008 ዓም)

በኢትዮጵያና ግብጽ መካከል በአባይ ግድብ ዙሪያ ሊካሄድ የነበረው ድርድር መዘግየትን ተከትሎ፣ የግብፁ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ ከሱዳን ጋር የሚመክር የልዑካን ቡድን ወደ ሃገሪቱ ላኩ።

በሃገሪቱ የመስኖ ልማት ሚኒስትር ሆሳም ሞግሃዚ የተመራው ይኸው ልዩ የልዑካን ቡድን፣ ከፕሬዚዳን አልሲሲ የተላከን ልዩ መልዕክት በመያዝ ከሱዳን ባለስልጣናት ጋር ለመምከር ካርቱም መግባቱን አል-አህራም የተሰኘ የግብጽ ጋዜጣ ዘግቧል።

ግብፅ በአባይ ግድብ ዙሪያ ከሱዳን ጋር የተናጥል ውይይትን ስታካሄድ ለመጀመሪያ ጊዘ ሲሆን ወደሃገሪቱ የተላከው ቡድንም ግድቡ በታችኛው የተፋሰስ ሃገራት ላይ በሚያመጣው ተፅዕኖ ዙሪያ ሰፊ ምክክርን እንደሚያካሄድ ተጠብቋል።

በኢትዮጵያ የተካሄደውን የካቢኔ ሹምሽር ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያ በግብፅ ሊካሄድ የነበረው ድርድር ለሌላ ጊዜ እንዲራዘም መጠየቋ ይታወሳል።

ይሁንና የግብፅ ባለስልጣናት የድርድሩ መዘግየት የሃገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ይጎዳል በማለት ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን በርካታ የግብፅ ባለስልጣናትም ጉዳዩ ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጀት እንዲወሰድ በማሳሰብ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

የግብፁ ፕሬዚደንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ በድርድሩ መዘግየት ያላቸውን ቅሬታ በመግለፅ የልዑካን ቡድናቸውን ወደ ጎረቤት ሱዳን እንደላኩ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በመገንባት ላይ ያለው የአባይ ግድብ እንዲያጠኑ ሁለት አለም አቀፍ ኩባንያዎች በሁለቱ ሃገራት ቢመረጡም አንደኛው ድርጅት ጥናቴን በገለልተኛነት ማከናወን አልቻልኩም በማለት ራሱን ማግለሉ ይታወሳል።

የኔዘርላንዱ ኩባንያ የወሰደውን ውሳኔ ተከትሎም ኢትዮጵያና ግብፅ ለአራት አመታት ያህል ጊዜ ሲያካሂዱ የቆየው ድርድር ለጊዜው ተቋርጦ ይገኛል።

ድርድሩ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ በግብፅ መዲና ይካሄዳል ተብሎ የነበረ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ጥያቄ ተከትሎ ድርድሩ በተያዘው ወር መጨረሻ እንዲካሄድ መወሰኑን የግብፅ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

ለአራት አመታት ያህል ኢትዮጵያን በመወከል የድርድሩ ተወካይ የነበሩት የውሃና ኤነርጂ ሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ ባለፈው ሳምንት ካሃላፊነታቸው ተነስተው በአማካሪነት መሾማቸው ይታወቃል።

አዲስ የተሾሙት የውሃና ኤነርጂ ሚኒስትር በሁለቱ ሀገራት መካከል በቀጣይ ይካሄዳል በተባለው ድርድር ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ግብፅ በበኩላ ጉዳዩ መጓተትን ያመጣል በሚል ቅሬታዋን እየገለጸች እንደሚገኝ አል-አህራም ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል።