የግብፁ ፕሬዚዳንት አል-ሲሲ በአባይ ጉዳይ ሊመክሩ አርብ አዲስ አበባ ኣንደሚገቡ የግብፅ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ

ኢሳት (ጥር 19 ፥ 2018)

የግብጹ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲ ሃገራቸው በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን ጥቅም ለማስጠበቅ ይረዳት ባሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በአዲስ አበባ እንደሚመክሩ የግብፅ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።

በቅርቡ በካርቱም ስምምነት የተደረገባቸው አዳዲስ የመግባቢያ ሃሳቦችም በዚሁ ውይይት ላይ ይነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አርብ እረፋድ ላይ አዲስ አበባ ይገነባሉ ተብለው የሚጠበቁት የግብፁ ፕሬዚዳንት በአፍሪካ ህብረት ልዩ የመሪዎች ጉባዔ ላይ የሚሳተፉ ሲሆን ከዚሁ ጉባኤ ጎን ለጎን ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በግድቡ ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የግብፅ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በሁለቱ ሃገራት መካከል በቅርቡ በሱዳን በተደረገው ስምምነት አሁንም ድረስ መነጋገሪያ  ሆኖ ይገኛል።

የግብፅ ባለስልጣናት በካርቱም የተደረሰው ስምምነት ግድቡን ውሃ የመሙላት ሂደት እንዲዘገይና ግድቡንም የመጎብኘት እንቅስቃሴ በሱንዳንና ግብፅ ፈቃድ ማግኘት እንዳለበት የሚያደርግ ነው ሲሉ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ይሁንና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከግብፅ ጋር የተደረሰ አዲስ ስምምነት የለም በማለት ማስተባበያን ሰጥተዋል።

ተጨማሪ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት የተቆጠቡት የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከግብፅ ጋር እየተደረገ ያለው ድርድር ቀጣይ መሆኑን አስታውቀዋል።

በሁለቱ ሃገራት የተቀጠሩ ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች በቀጣዩ ወር ለዘጠኝ ወር ያህል የሚቆይ ጥናትን የሚጀምሩ ሲሆን የጥናቱ ውጤትም ይግባኝ የሌለው ነው ተብሏል።

የአባይ ግድብ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ሊያመጣ ይችላል የተባለ ስጋት በጥናቱ ውስጥ በዋነኛነት የተካተተ ሲሆን ግብፅ የወንዙ ፍሰት ላይ የሚደርስ ተፅዕኖም  እንዲካተት ማድረጓን የግብፅ ባለስልጣናት ገልጸዋል።